በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በቤቱ ሳለህ የእግዚአብሔርን ውለታ አለመርሳት
አዕምሮ ያላቸው ፍጡራን ሰዎች በእያንዳንዱ ኹኔታ ያሉትን አያሌ አማራጮችን የመመልክት ኃይል አላቸው፡፡ ፍጹም ኹኔታዎችን በማየት ፈንታ ተቃራኒ የኾኑትን ይፈልጋሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን እንዲህ በማለት ይናገራል "ወደ ሕይወት ልትገባ ብትወድ ትዕዛዛትን ጠብቅ" ይለናል ማቴ 19÷17፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቤት ሳለህ ውለታውን ሳትረሳና ሳትወጣ ለመኖር ከፈለግኽ የሚከተሉትን ተጥቦች በጥልቀት መርምራቸው፡፡1) በኑፋቄ ወይም በክኅደት ትምህርት እንዳትጠመድ
2) ራስህን በትክክል ማወቅ ግልጽነትና ታማኝነት ያስፈልጋል
3) ራስህን በሌሎች ምዕመን ዓይን ለማየት መሞከር
4) በራስህ ዓይኖች በተጨባጭ ራስህን ተመልከት
5) ራስህን በሌሎች ሰዎች ወይም ምዕመን ቦታ አስቀምጥ
[1]. በመልካም ሳይኾንላቸው ሲቀር በዚያ ግዜ የማይታገሱ ችላ ያሉም ብዙዎች ናቸው፡፡ ነገርግን በወደደ ግዜ የወደደውንም ያህል ለወደደውም ለርሱ ደስ እንዲለውና በመጠኑም መሥጠትና መለገስ እንዲኹም ማጽናናት የልዑል እግዚአብሔር ብቻ ነው እንጂ መንገዱ ዘወትር በሰው ሥልጣን አይሆንም፡፡ የማይጠነቀቁ አንዳንድ ከእውቀት ፍርድ ይልቅ የልቡናቸውን ፈቃድ ተከትለው የታናሽነታቸውን መጠን ሳይገምቱ ይበልጥ ማድረግን ስለፈለጉ በመንፈሳዊነት ጸጋ ምክንያት ተሰናክለው ራሳቸውን አጠፉ፡፡አምላክም ከፈቀደላቸው ይበልጥ ታላላቅ ማዕረጎችን ፈልገዋልና ስለዚህ ጸጋቸውን ፈጥነው አላጠፉ አምላክም አጠፋባቸው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁላ ለመዳን የተሰጠህን የመንፈሳዊነት ጸጋን መሠወር ራስህንም ወደላይ አለማውጣት ስለዚህም ብዙ አለመናገር ብዙም አለመገመት ይልቁንም ራስህን መናቅ ሳይገባህም ስለ ተሰጠችህ ጸጋ መፍራት ላንተ ጥቅም ነው፡፡ ሓዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም"በተሰጠህ ጸጋ እግዚአብሔርን አገልግል በማለት ተናግሯልና" ሮሜ 12÷7፡፡
በመንፈሳውያን ሥራዎች በመለኮታዊ ሐሳብም /ፍቃድ/ ተጣብቆ መኖር ባልቻልህ ግዜ ስለ ሥጋ ሸክም ለሥጋ ብዙ ግዜ ማልቀስ ይገባሃል ? አባ እንጦስም "ሁልግዜ ኃጥኣትህን እያሰብክ ንሰሓ ግባ" በማለት ተናግረዋልና፡፡ በዚያን ግዜ ወደ ትሕትና ሥራዎች መጠጋት ይሻልሃል፡፡ በመልካሞች ሥራዎች ራስህን ማደስ ማስተካከልና በጽናት በመታመን መጠበቅ ይሻላል፡፡
በትእዛዝ መቆም ከሹማምንት በታች መኖር እንደ ራስ ፈቃድምአለመሆን እጅግ ታላቅ ነገር ነው፡፡ከማዘዝ ይልቅ በመታዘዝ መኖር እጅግ የሚሻል ነገር ነው፡፡ ምክርን ከመስጠት ይልቅ ምክርን መስማትና መቀበል እጅግ እረፍት እንደሆነ ብዙ ግዜ ሰማሁ፡፡ ደግሞ የሁሉ ሐሳብ መልካም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ነገሩን ምክንያቱ ሲሰማማ የሌሎችን አለመቀበል የትዕቢት ወይም የእምቢተኝነት ምልክት ነው፡፡
Ø ከሌሎች ጋር መስማማትና ፍቅር ማድረግ ብትፈልግ ራስህን በብዙ ማዋረድ እንድትማር ይገባሃል፡፡ በገዳም ወይም በማኅበር በዚያም ያለ ጠብ መኖር እስከሞትም ድረስ የታመነ ሁኖ ጠንቶ መኖር ታናሽ ነገር አይደለም፡፡ በዚያም በመልካም የሚኖር በመልካም የሚፈጽም ብፁዕ ነው፡፡ በሚገባ መኖርና በመንፈሳዊ ኃይልን እየጨመርህ መሄድ ብትፈልግ በምድር ላይ ራስህን እንደ ስደተኛና እንደ መንገደኛ አድርግ፡፡
Ø መንፈሳዊት ነፋስ በዝምታና በዕረፍት ትጠቅማለች የተሸሸገም የቅዱሳትመጻሕፍት ምሥጢርን ትማራለች፡፡
Ø የመንፈሳዊነት ጸጋን መጨመር ብትፈልግ እግዚአብሔርን በመፍራት ራስህንም ለማይገባ ደስታ አሳልፈህ አትስጥ፡፡ ራስህንም ለንሰሐ አቅርብ መንፈሳዊነትን ታገኛለህ፡፡
Ø በመልካም ሕሊና እግዚአብሔርን ከመፍራት በቀር እውነተኛ ነጻነትና መልካም ደስታ የለም፡፡
Ø ራስህን ወደ እግዚአብሔር ባትመልስ ባለህበትና በዞርህበት ሁሉ ምስኪን ትሆናለህ፡፡
መንፈሳዊኃይልን ለመጨመር ተስፋን አትቁረጥ ገና ጊዜና ሰዓት አለህ፡፡ ስለምን ፈቃድህን ለነገ ታዘገያለህ ተነሣ አሁን ዠምር አሁን የማድረግ ጊዜ ነው አሁን የመዋጋት ጊዜ ነው አሁን አኗኗርን የማረም ግዜ ነው በል ስትታመምና ስትጨነቅ በዚያን የትሩፋት ጊዜ ነው እንዳትቀዘቅዝ ለእሳትና በውሃ ማለፍ ይገባሃል፡፡ ኃይልን ባታደርግ ክፋትን አታሸንፍም፡፡ይህንን ደካማ ሥጋ ተሸክመን ሳለን ያለ ኃጢያት መሆን ያለመሰልቸትና ያለሕማም መኖር አንችልም፡፡ ከመከራ ሁሉ ልናርፍ በወደድን ነበር፡ ነገር ግን በኃጢያት ንጽሕናን አጥፍተናልና እውነተኛ ደስታን ደግሞ አጠፋን፡፡ስለዚህ ይህች ኃጢኣት እስካልፍ ድረስ መታገሥ የእግዚአብሔርንም ምሕረት መጠበቅ ይገባል፡፡
ነገር ግን በነገር ሁሉ የሚጠቅምህን ያዝ፡፡ መልካም አብነት ብታይ ወይም ብትሰማ እንድትከተለው ፈቃድን አድርግ፡፡ የሚነቀፍ ነገር ብታይ እንደርሱ እንዳታደርግ ተጠንቀቅ ፡፡ ወይም አንዳንድ ግዜ ያደረግህ ብትሆን ቶሎ ከርሱ እንድነጻ ትጋ፡፡ ዓይንህ ሌሎችን እንደሚመለከት እንዲህ ሌሎች ደግሞ ይመለከቱሀል፡፡ መልካም ጠባይ የሚደርጉንና ሥራትንም ሁሉ የሚጠብቁ ትጉዎችንና መንፈሳውያን ወንድሞችን ማየት ምንኛ ደስ የሚያሰኝና ያማረ ነው፡፡ የተጠሩበትን የማይሠሩ ሥርዓትንም አጠፍተው የሚኖሩትን ማየት ምንኛ የሚያሳዝንና የሚያስለቅስ ነው፡፡ የተጠራበትን ቸል ማለት ሥራውንም ትቶ ያልሆነን ነገር ማሰብና መሥራት ምንኛ የሚጎዳ ነው፡፡
በመልካምና በሥርዓት የሚኖርመነኩሴ የታዘዘውን ሁሉ በመልካም ይቀበላል ይፈጽማልም፡፡ በጭንቀት ላይ ጭንቀት ይጨምርበታል፡፡ በሁሉም ወገን መከራን ያገኛል ከገዳም ወይም ከሥርዓት ወጥቶ የሚኖር መነኩሴ ጥልቅ ገደል ተከፍቶለታል፡፡ አንዱ ወይም ሌላው ያሳዝነዋልና የላላንና የተተወን ሥራን የሚሻ ዘወትር በጭንቀ ይኖራል፡፡
በገዳማቸው ሥራት በብርቱ የተጨነቁ ብዙ መነኮሳት እንዲህ ያደርጋሉ ብዙ ግዜ መጥተው አይዞሩም በጭንቀ ይኖራሉ እንደ ድኃ ይመገባሉ፤ ብዙ ይሰራሉ፤ ጥቂትም ይንገራሉ፤ ብዙ ጊዜ ይነቃሉ ማለዳም ይነሣሉ፤ ጸሎትንም ያረዝማሉ፤ መጻሕፍትንም ብዙ ጊዜ ይመለከታሉ በሥራትም ሁሉ ራሳቸውን ይጠብቃሉ በሌሊት በቀን ሁሉ ጊዜ ሰዓት ሳይወስኑና ሳይገድሉ የቅዱስ ዳዊትን መዝሙርንና ቅዱስ ያሬድን የዜማ መጽሕፍትን በመግለጥና በማዜም ዘወትር እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያለ የመነኮሳት ሕይወት ለእግዚአብሔር ራሳቸውን በማስገዛት ዜማን በማዜም ሥርዓትን በመጠበቅና በማስጠበቅ ሲኖሩ አንተ በዚህ በተቀደሰ ሥራማኽል ሀሴትን ብታደርግ ነውር አይደለምን?
[2]. ራስሕን በትክክል ማወቅ ግልጽነትና ታማኝነት ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብም በመልዕክቱ ላይ 'ወእመሰተቃንአ መሪር ወካሕድ ብክሙ ውስተ ልብክሙ ኢትትመክሑ ወኢተሐስውዎ ለጽድቅ - ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኝነት በልባችኹ ቢኖርባችኹ አትመኩ በእውነት ላይ አትዋሹ' በማለት አስተምሯል ያዕ. 3÷14፡፡ አገልግሎትም ኾነ በመንፈሳዊ ሕይወት ዙሪያ ግልጽነትና ታማኝነት አስፈላጊ ነው፡፡ በታማኝነትና በግልጽነት ዙሪያ ወይም መኀከል መስማማት መወያየት መተማመን መመካከርም ያስፈልጋል፡፡ይኽንንም በተመለከተ ሐዋርያው ያዕቆብ እንዲኽ በማለት ይናገራል 'እምአይቴ ለክሙ ፀብእ ወቀትል አኮኑ እምዝየእም አፍቅሮ ዝሙት ዘይትገበር ውስተ አንጎዕክሙ፡፡ትፈትውሂ ወኢትረክቡ፡፡ ትትቃተሉሂ ወትትቃንኡሂ ወኢትክሉ ረኪበ፡፡ ትትበአሉሂ ወትትፃብኡሂ ወኢትረክቡ እስመ ኢትስእሉ፡፡ ወትስእሉሂ ወኢይሁቡክሙ እስመ ለእኪት ትስእሉ ለዝሙትክሙ ከመ ተሀሉ -በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችኹ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚኽ ከምኞቶቻችኹ አይደሉምን?ትመኛላችኹ ትዋጉማላችኹ ለእናንተ አይኾንም ፥ ትገድላላችሁ በብርቱም ትፈልጋላችሁ ልግኙም አትችሉም ፥ትጣላላችሁትዋጉማላችሁ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም---' ያዕ. 14÷1-3 በማለት አብራርቶና ዘርዝሮ አስቀምጦታል፡፡ ነገር ግን እነዚህንነገሮች ካላካተትክ አንተ ማነህ?የምታደርገው ነገር በሙሉ ለቅድስናና ለሕይወት የማይኾንና የማይለወጥ ፍሬ የሚያፈራ አበባም የሚያብብ በሰው ልጅ ዓይን ውስጥ የማትገባና የማትታይ የማትመሰገን ከኾነ የአንተ በቤቱ መመላለስህ ምን ይረባል ምንስ ይጠቅማል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መጥምቁ ዮሐንስን 'ዝንቱ ውእቱ ማኀቶት ዘየኀቱ ወያበርኅ - የሚነድና የሚያበራ ፋና ነበር---'ይለው አልነበር፡፡ ዮሐ.5÷35 የምናደርገውን የምንሠራውን ነገር በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር ልናደርገው ይገባል፡፡ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ከኾነ በዚኹ በዮሐንስ ወንጌል ላይ 'እግዚአብሔርመንፈስ ነው÷የሚያስግድሉትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል' ዮሐ.4÷24 በማለት ተናግሯል፡፡ የአንተ አገልግሎትም ኾነ አምልኮ በመንፈስ ሲኾን ያስፈልጋል፡፡
ነገር ግን በሕይወትህ ውስጥ ለሌላው የምታሳያቸው ጥላቻዎች በልጅነት የተወረሱናቸው?ወይስ ከግዜ በኃላ ያመጣሃቸው?በእርግጥ አንድ ሰው ከጸሎት ሲርቅ የሞት መሣሪያውን መሥራት ይዠምራል ይላሉ የቤተ እግዚአብሔር አባቶች፡፡ አንተም ብትኾን ይኽ ነገር የሚታይብህ ይመስላል፡፡ ሐዋርያው ቀወዱስ ጴጥሮስም በአንደኛ መልዕክቱ ላይ'ወኩኑ ከመእለ ይእዜ ተወልዱ ሕጻናት ወአፍቅሩ ሐሊበ ነባቤ ዘአልቦቱ ቱስሕት ከመቦቱ ትልሀቁ ለድኂን- አኹን እንደተወለዱ ሕጻናት ተንኮል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ' በማለት አስቀምጦታል 1ጴጥ.2÷2፡፡ እስቲ በዚኽ ቃል ራስሕን ተመልከት ያልተመለክትክ እንደኾነ ግን ኋላ የምታስበውና የምትጨነቅው ነገር ቢኖር ቆዳኽ ነጭጥቁር እንዲኾንልኽ ዓመቱን በሙሉ ስፓርት በመሥራት ባሳለፍኩ ብለኽ ትመኛለኽ? ወይስ ደግሞ ቆዳኽ ቡናማ ወይም ጥቁር ስለኾነ ነጭ በኾነልኝ ብለኽ ትመኛለኽ? ጥቁር ቆንጆ፥ ነጭነት ደግሞ በሽተኛና የገረጣ ነውን? ነጭሲባል ሃብታም፥ ጥቁር ሲባል ደግሞ ደሃ ነውን? ጥቁር ወርቅ ሲሆን ነጭ ደግሞ ወዳቂ ነውን? በማለት ኀሳብክ የተዘበራረቀና የተመሰቃቀለብህ ይኾንብል፡፡ የአንተ አስተሳሰብም ከዚህና ከነዚህ መሰሎች አይዘሉም ወይም አያልፉም፡፡ ነገር ግን ራስን በትክክል ማወቅ እያንዳንዱ በምድር ላይ ሰብአዊ ፍጡር በዚህ ዓለም ችሎታው ለመጠቀም እኩል መብት ያለው ሰው መሆኑን መገንዘብ ማለት ነው፡፡
ራስህን በትክክል ማወቅ የቆዳ ቀለም÷የትውልድ ቦታ÷ሃይማኖታዊ እምነት÷ፆታ ኀብትና አስተዋይነት የሰው ልጅ የክብር መለኪያ አለመኾናቸውን መገንዘብ ማለት ነው፡፡
የራስህን ማንነት በትክክል ሳትገነዘብ ስለወንድምህ ማንነት አታውራ፡፡ መጽሐፍስ ይህን ነገር አበክሮ ይናገር የለምን 'ወርእስክሙ አመክሩ ለእመ ሀለውክሙ በሃይማኖት ወርእስክሙ ሕቱ- በሃይማኖት ስትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ'2ቆሮ.13÷5 በማለት አስቀምጦታል፡፡ ሐዋርያው ይህን ያለው ራሱን ሳይመረምር ቀርቶ አይደለም ፡፡ የራሱን ማንነት አስቀድሞ /ከመናገሩ በፊት/ ራሱን አግባብ ባለው መንገድ መርምሮ ስለራሱ ኃጥያት ንሰሐ ገብቶ ተጸጽቶ ነው ስለኛ ኃጢያት ደግሞ ተጨንቆ ነው ይህን የጻፈልን፡፡ አንተ ግን ይህን ልትናገር ስትል አስቀድመህ የነበርክበትን አለመርሳትም አስፈላጊ ነው፡፡ አስቀድመህ የነበርክበትን ሕይወት በአሁኑ ሰዓት አለማስታወስህ ድንገት በቤቱ አገልጋይ አስቀዳሽ÷ የሰርክ ጉባዔ ተማሪ÷አስተማሪ÷ ቀዳሽ÷ቡራኬ ሰጪ÷የሰንበት ተማሪ ÷ወይም ምእመን ልትኾን ትችላለህ፡፡ ነገር ግን አባ እንጦንስ 'ኃጢያትህን እያሰብክ ሁልጊዜ ንሰሐ ግባ' ይላሉ፡፡ አንተም ሆንክ ሌላ ምእመን በቤቱ ሳላችሁ የሚገባችሁን ÷ የድርሻችሁን ÷ የጸጋችሁን ÷ ያቅማችሁን ያህል ልታገለግሉ ልትመላለሱ ይገባችኋል ፡፡ ሐዋርያው በሮሜ መልዕክቱ 12÷7 ላይ'ሁሉም በተሰጠው ጸጋ እግዚአብሔር ያገልግል---' በማለት ተናግሯል፡፡
[3]. ራስሕን በሌሎች ምዕመን ዓይን ለማየት መሞከር አለብህ- ይህን ርእስ ልብ ብለህ ለመመልከትና ለማየት ሞክር፡፡ እኔ ልጆቼን ብሆን ብለህ ገምት እኔ የትዳር ጋደኛዬን ብሆን ብለህ ገምት፡፡ ወደ አንተ ክፍል ወይም ቢሮ ስትገባ የሚመለክትህ ሰው ሁሉ ስለአንተ ኹለት ነገር ያስባል፡፡ ይኸውም 'በደንብ የለበስክና በራስ የምትተማመን' ወይም ደግሞ'ትዕቢተኛ ቁጡ' ሆነህ ትታያለህ፡፡ አንተስ የትኛው ቢሆንልህ ትፈልጋለህ ለምንስ መርጥከው?‹ነገር ግን እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፡፡ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ፡፡› በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጻፈው መልዕክቱ ላይ አስቀምጦታል ሮሜ. 8 ÷ 13፡፡
[4]. በራስህ ዓይኖች በተጨባጭ ራስህን ተመልክት - ይህ ለኹላችንም ቢሆን መናገሩ ከማድረጉ የቀለለ ኾኖ ይገኛል፡፡ ይህን ተግባር ራስኽን ለመፈተን ከፈለግክ ኹለት ዓይኖችህን ለማየት የሚችሉበትን ቀዳዳ ባለው የኪስ ወረቀት ራስህን ሸፍነህ ሙሉ ቁመት ባለው መስታወት ፊት ለመቆም ሞክር፡፡ከፊት ከኃላህና ከጎንህ ራስህን ተመልከት በአዕምሮ ውስጥ ያለውን ወይም የተከማቸውን የኃጢያት ሽክም በሙሉ በመስታወት ውስጥ ላለው ምስልህ አውራው፡፡ ያን ግዜ በጣም የምታውቀው ፊትህ በኪስ ወረቀት ሲሸፈን በልብህ ያለው ኃጢአትህ ያንተ አይመስልህም፡፡ እውነትን ፈልግ÷እውነትም ተናገር የንግድ ማስታወቂያዎችን ጊዜያዊ ፋሽኖች ቁጥር ስፍር ከሌላቸው የስስት ምርኮኞች አንዱ እንዳያደርጉህ ተጠንቀቅ፡፡ ልጆችንና አረጋውያንን አትርሳ፡፡ ያላቸውን ልዩ ችሎታ ልብ አድርገህ አስተውል ፡፡ ምን ኃሳብና ስሜት እንዳላቸው ጠይቅ በተጨማሪም ሽምግልና ወይም አረጋዊነት አይቀሬ እንደሆነ አስታውስ፡፡ አረጋዊነት ብቸኝነት የተሞላበት ወይም ደግሞ አስደናቂ ግዜ ሊኾን ይችላል፡፡ ብዙ የምታከናውናቸው ሥራዎች÷ግቦች÷ ትኩረቶች ካሉ አረጋዊያን የቤተክርስቲያኒቷ ዓይኖች ናቸውና ይህን አትርሳ፡፡ ነገሩ ይህን መመልከት የምትችለው ራስን በትክክል ከማወቅ የተነሳ የሚመጣ ነገር ነው፡፡መዝ. 126÷13 ማቴ.19÷1
[5]. ራስሕን በሌሎች ሰዎች ወይም ምዕመን ቦታ አስቀምጥ- ሌሎች ሰዎች ያላቸውን ስሜት ለማወቅ ሞክር፡፡ ሒስ ወይም ፍርድከመስጠትህ በፊት ከየት እንደመጡ ተገንዘብ ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በድርሰቱ ላይ'የወንድምህን ኃጢያት መሸፈንና የእርሱን ኃጢያት እንደራስህ አድርገህ በእርሱ ፈንታ መሞት ካልቻልክ ቢያንስ ቢያንስ ስለኃጢአቱ አትፍረድበት'በማለት ተናግሯል ፡፡ የምታውቀውም ሆነ የምታገኘው ሰው ሁሉ ስሜት ሊኖርህ ባይችልም የማናቸውንም ፍጡር ስሜት ማስተናገድህን አረጋግጥ፡፡ ይህ ራስህን በትክክል እንድታውቅ የሚረዳ ቁልፍ ነገር ነውና፡፡ ይህ ሁላ ግን የሚሆነው በጸሎት÷ በስግደት÷በጾም÷በትእግስት ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ለነዚህ ሁሉ መሠረቱ ደግሞ የወንጌላቱ ጸሐፊዎችን ትምህርት ልብ ልትል ይገባል ቃሉንም እንዲህ ለማለት ይናገራሉ፡፡
'ወንድሞቼ በሰማያት ያለውን ፈቃድ የሚያደርጉ ሁሉ እነርሱ ወንድሞቼም እህቶቼም ናቸውና'ብለዋል ማቴ. 12÷50፣ ማቴ.26÷29፣ ዮሐ.4÷7፣ዮሐ.15÷5-7፡፡እነዚህን ሁላ ግን የምትረሳውና ከመንገዱ ፈቀቅ በምትልበት ሰዓት የእግዚአብሔርን መልእክት ማስታወስና መንገንዘብ እንዲሁም መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከእነዚህ ነገሮች ፈቀቅ የምትለው የእግዚአብሔርን ውለታ መርሳት በመጣና ባሰብክ ሰዓት/ወቅት/ ነው፡፡ ውለታን መርሳት ማለት ደግሞ አስቀድሞ በቤቱ ከመምጣትህ በፊት÷ንሰሐ ከመግባትህ በፊት÷ ለአገልግሎት ከመሠማራትህ በፊት የነበርክበትን የዓለምን ኑሮ አስተውለህ ተራመድ፡፡ እነዚህን ነገሮች በሙሉ ያለማስተዋል ችግሩ ከቤቱ መራቅ ከቤቱ መሸሽ ለኃጢአት ቦታ መስጠት የመሳሰሉትን ነገሮች በሚከሰቱበት ወቅት ነውና የእግዚአብሔርን ውለታ ሳትረሳ ለመንፈሳዊ ሕይወት ለቅድስና ለበለከት እንቅፋቶች ናቸውና በሕይወት ሁሉ ላይ ውለታውን ሳትረሳ በቤቱ ጸንተህ ለመገኘት ሞክር፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!
ኢዮኤል ሰሎሞን
ጥቅምት 2004 ዓ.ም
ጥቅምት 2004 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment