በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ አሜን
ሥላሴ ጥንትና ፍጻሜ በሌለው ዘመን በአንድነት በሦስትነት ሲመሰገኑ ይኖራሉ፡፡ንባርኮ ለአብ ወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እናዳሉ ሠለስቱ ደቂቅ ንባርኮ ብለው አንድነታቸውን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ብለው ሦስትነታቸውን ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ ለዓለም ጥለው ጥንትና ፍጻሜ የሌላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሤለሱ በአካላት ወይትወሀዱ በመለኮት - በአካል ሦስት በመለኮት አንድ ይኾናሉ፤ እንዳለ ዮሓንስ ዘአንጾኪያ ተናግሯል፡፡ ሥላሴ አንድ ሲኾኑ ሦስት፤ሦስት ሲኾኑ አንድ ናቸው፡፡ ከሃይማኖት የወጡ የሰባልዮስ ወገኖች እንደሚሉት አንድ አካል አይባሉም፤በሦስቱ አካላት አንድ መለኮት አለ ይባላል እንጂ፤እንዳለ ባስልዮስ ዘቂሳርያ፡፡ ሥላሴ በተዋሕዶ ወተዋህዶ በሥላሴ ተጋብኦ በተከፍሎ ወተከፍሎ በተጋብኦ ሱስንዮስ እንደተናገረ፡፡
ቅድስት ሥላሴ የማይቀዳደሙ መሆናቸውን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን እንደምታስተምረን ከሆነ ሰውና ፀሐይ ፤ እሳትና ውሃ ናቸው በማለት ታስተምራለች፡፡ሥላሴ አዳምን ' ንግበር ሰብኣ በአርአያነ ወበአምሳሊነ- ሰውን በመልካችን እንደምሳሌያችን እንፍጠር ' ዘፍ.1÷26 ብለው በፈጠሩት ጊዜ ተገኘ እንጂ አንዱ ቀድሞ ወደኃላ የተገኘ የለም ሥላሴም ኣብ ሳይቀድም ወልድን መንፈስ ቅዱስን አስገኘ፡፡ ወልድም ሳይከተል ከኣብ ተወለደ መንፈስ ቅዱስም ተለይቶ ሳይቀር ከኣብ ሠረፀ አብ አባት ነኝ ብሎ አልቀደመም፡፡ ወልድም ልጅ ነኝ ብሎ አልተከተለም መንፈስ ቅዱስም ሠራፂ ነኝ ብሎ አልቀረም፡፡ ኢሀሎ አብ አሓተ ሰዓተ- አብ ያለወልድና ያለመንፈስ ቅዱስ የነበረበት ጊዜ የለም፡፡ወልድም ያለ አብና ያለ መንፈስ ቅዱስ የነበረበት ጊዜ የለም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ያለ አብና ያለወልድ የነበረበት ጊዜ የለም እናዳለ ሳዊሮስ
ኹለት ጆሮዎች ከራስ ተዋሕደው ሳሉ፤ቢሰሙ እንጂ ተለያይተው እንደማይሰሙ፤ኹለት ዓይን ከግንባር ተዋሕደው ሳሉ ቢያዩ እንጂ ተለያይተው እንደማያዩ ፤ ኹለት እጅ ከደረት ተዋሕደው ሳሉ ቢይዙ እንጂ ተለያይተው እንደማይዙ ፤ኹለት እስትፋስም ልብ ተዋሕደው ሳሉ ቃል ቢናገር እስትንፋስም ቢተነፍስ እንጂ ተለያይተው ቃል እንደማይናገር ÷ እስትንፋስ እንደማይተነፍስ አብ ልብነት ገንዘቤ ከሆነ ብሎ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ህልው ሆኖ ያስባል እንጂ ተለይቶ አያስብም፤ ወልድም ቃልነት ነባቢት ገንዘቤ ከሆነ ብሎ በአብና በመንፈስ ቅዱስ ሕልው ሆኖ ይናገራል እንጂ ተለይቶ አይናገርም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ሕይወትነት ገንዘቤ ከሆነ ብሎ በአብና በወልድ ህልው (ሕያው) ሆኖ ይኖራል እንጂ አይለይም፡፡
ለፀሐይም ሦስትነት አለው ክበቡ ብርሃኑ ሙቀቱ ከክበቡ÷ብርሃኑና ሙቀቱ ይወጣሉ፡፡ ሲለወጡ ግን ክበቡ ቀድሞ ብርሃኑ ተከትሎ ሙቀቱ በኃላ ቀርቶ አይደለም በፀሐይ ሦስትነት መቀዳደም የለበትም÷ሳይቀድምአንድ ጊዜ ይወጣል ÷ይገባል ክበቡ ብርሃኑ ሙቀቱ በምን ይታወቃል ቢሉ ፀሐይ ወጣ ገባ ባሉ ጊዜ ክበቡን መናገር ነው ብርሃኑም ጨለማውን በመራቁ የተሠወረውን በመግለጡ ይታወቃል ሙቀቱም ፀሐይ ወጣ ልሙቅ ማለት አለና የበረደዉን በማሞቅ የረጠበውን በማድረቅ ይታወቃል፡፡ እንደ ክበቡ አብ -እንደ ብርሃኑ ወልድ-እንደ ሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ ነዉ፡፡ ከክበቡ ብርሃንና ሙቀት እንዲወጡ ከአብም ወልድ ተወለደ መንፈስ ቅዱስ ሠረፀ፡፡
በፀሐይ ሦስትነት መቀዳደም እንደሌለበት በሥላሴም ሦስትነት መቀዳደም የለባቸውም፡፡ ብርሃንና ሙቀትን ክበብ እንደማይቀድማቸው ወልድንና መንፈስ ቅዱስንም አብ አይቀድማቸውም፡፡ ክበቡን ብርሃኑን ሙቀቱን አንድ ፀሓይ እንዳሉ መጻሕፍት አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስን አንድ አምላክ ብለን እናምናለን፡፡'ወውስተ ፀሓይ ሤመጽላሎቶ- አንድነቱን በፀሐይ መሰለ' ብሎ ክቡር ዳዊት እንደተናገረ መዝ.18÷5 አቡየ ፀሓይ ወኣነ ብርሃን ወመንፈስ ቅዱስ ዋዕይ- ኣባቴ ፀሐይ÷እኔ ብርሃን ÷ሕይወቴ መንፈስ ቅዱስ ሙቀት ነን አለ ብሎ ርቱዓ ሃይማኖት እንደተናገረ፡፡
ለእሣት ሦስት ነገር አለው ፍሙ ነበልባሉ ዋዕዩ ከፍሕሙ ነበልባልና ዋዕይ ይወጣሉ፡፡ ስለ ወጡ ግን ፍሕሙ ቀድሞት ነበልባሉ ተከትሎት ዋዕዩ በኃላ ቀርቶ አይደለም በእሳት ሦስትነት መቀዳደም የለበትም ሳይቀዳደሙ አንድ ጊዜ ይገኛል÷ፍሕሙ ነበልባሉ ዋዕዩ በምን ይታወቃል ቢሉ ÷እሳት ልጫር ላምጣ ባሉ ጊዜ ፍሕሙን መናገር ነው፡፡ብርሃኑም እሳት አበራ÷መብራት አያለኹ ማለት አለና ጨለማውን በማራቁ የተሠወረውን በመግለጡ ይታወቃል÷ ዋዕዩም እሳት ፈጀኝ ተኮሰኝ ማለት አለና ÷የበረደውን ለማሞቁ የረጠበውን በማድረቁ ይታወቃል÷እንደ ፍሕሙ አብ እንደ ነበልባሉ ወልድ እንደ ዋዕዩ መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ ከፍሕሙ ነበልብልና ዋዕይ እንዲወጡ ከአብም ወልድ ተወለደ÷ መንፈስ ቅዱስ ሠረፀ በእሳት ሦስትነት መቀዳደም እንደሌለበት በሥላሴም ሦስትነት መቀዳደም የለባቸውም÷ፍሕሙን ነበልባሉን ዋዕዩን አንድ እሳት መጻሕፍት፡፡
አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም÷አንድ አምላክ አንድ መለኮት ብለን እናምናለን፡፡አቡየ እሳት ወአነ ነበልባል ወመንፈስ ቅዱስ ዋዕይ - አባቴ እሳት እኔ ነበልባል መንፈስቅዱስ ዋዕይ ነው፡፡ አለ' እንዳለ ርቱዓ ሃይማኖት
ለውኃም ሦስትነት አለው ስፋሐቱ÷ርጥበቱ ÷ሁከቱ ነው፡፡ ከስፋሐቱ ርጥበትና ሁከት ይወጣሉ፡፡ ስለ አወጣጡ ግን ስፋሐቱ ቀድሞ ርጥበቱ ተከትሎ ሁከቱ በኃላ ቀርቶ አይደለም፡፡ በውሀ ሦስትነት መቀዳደም የለበትም አንድ ግዜ ይቀዳል፡፡ ስፋሐቱ ርጥበቱ ሁከቱ በምን ይታወቃል ቢሉ÷ውሃ ልቅዳ ላምጣ ባሉ ጊዜ ስፋሐቱን መናገር ነው ርጥበቱ ውሃ ጠማኝ ልጠጣ ማለት አለና (ጥ)ጽምፅን በማብረዱ እሳትን በማጥፋቱ ይታወቃል፡፡ ሁከቱም ውሃ ሄደ መጣ ማለት አለና በመሄዱ በመናወጡ ይታወቃል፡፡እንደ ስፋቱ- አብ እንደ ርጥበቱ- ወልድ እንደ ሁከቱ- መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡
ከስፋቱፍጥበትና ሁከት እንዲወጡ ከአብም ወልድ ተወለደ መንፈስ ቅዱስ ሠረፀ ለውሀ ሦስትነት መቀዳደም እንደሌለበት÷በሥላሴም ሦስትነት መቀዳደም የለባቸውም፡፡ ርጥበትና ሁከትን ስፍሐት እንደማይቀድማቸው ወልድንና መንፈስቅዱስን አብ አይቀድማቸውም፡፡ ስፍሐቱን ርጥበቱን ሁለቱን አንድ ውሀ እንዳሉ መጻሕፍት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስን አንድ አምላክ ብለን እናምናለን፡፡
ነጽርኬ ዘተብህለ ለእንተ አበ ኩሉ መሰልዎ በዛቲ ባሕር እንተ ትትገሠሥ የሁሉ አባት አብን በሚዳሰስ ባሕር እንደ መሰሉት የባሕርይ ስግደት የሚገባው÷ ወልድንም በውሃ ርጥበት እንደመሰሉት ÷ በኹሉ ዘንድ የሚመሰገን መንፈስ ቅዱስንም በጥልቀት ባሕር የውሃ መናወጽ እንደመሰሉት አስተውል÷እንዳለ አረጋዊ መንፈሳዊ ይህም ቅሉ ምሳሌ ዘየሐፅፅ ነውእንጂ በቂ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ መጻሕፍት የተናገሩትን ምስክር አድርገን የሥላሴን አንድነትን ሦስትነትን እንናገራለን፡፡
በኦሪት አዳም ኮነ ከመ አሓዱ እምኔነ - እነኾ አዳሞ መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ኾነ ብሏል ዘፋ. 3÷ 22አዳም ኮነ ከመ አሓዱ ማለት አንድነታቸውን እምኔነ በማለቱ ሦስትነታቸውን ይጠይቃል፡፡ ደግሞም እነ ውእቱ አምላክ አብርሃም ወአምላክ ይሰሓቅ ወአምላክ ያዕቆብ ÷ የአብርሃም አምላክ የይስሓቅ አምላክ የያዕቆብ አምላክ እኔ ነኝ ብሏል ማቴ፣22÷32 ሦስት ጊዜ አምላክ አምላክ አምላክ ማለቱ ሦስትነታቸውን ኣነ ውእቱ ማለቱ አንድነታቸውን ይጠይቃል፡፡ ኢሳያስም ሲመሰገኑ ሰምቶ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር ፀባኦት ፍጹም ምሉዕ ሰማያት ወምድረ ቅድሳተ ስብሐቲከ ÷ ልዩ አሸናፊ እግዚአብሔር ምስጋናህ በሰማይና በምድር የመላ ነው ብሏል፡፡
ሦስት ጊዜ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ማለቱ ሦስትነታቸውን ቅድሳተ ስብሐቲከ ለማለቱ አንድነታቸውን ያጠይቃል፡፡ ሠለስቱ መዕተ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሓዱ አምላክ ብለዋል፡፡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ማለታቸው ሦስትነታቸውን አንድ አምላክ በማለታቸው አንድነታቸውን ያጠይቃል፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህንን ምሳሌ ስትሰጥ መከፋፈል መለያየት መቀዳደም እንደማይኖርበት ተጠንቅቃ ተጠባ የሰጠችው (የመሰለችው) ነው፡፡ ማንም በገዛ ፈቃዱ ሊከፋፈል ሊያበላልጥ ሊያወዳድር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሥላሴን መከፋፈል ማወዳደር ማሽቀዳደም ማለት መንፈስ ቅዱስን እንደመካድና እንደመስደብ ነው፡፡መጽሓፍስ እንዲህ ይል የለ- ስድብና ኃጢአት ስርየት አላት መንፈስ ቅዱስን ግን የሰደበ ስርየት የለውም፡፡ ተብሎ ተጽፏል፡፡
ቅዱሳን አባቶች እንደሚያስተምሩን ከኾነ ቅድስት ሥላሴ ቦታ ሳይወርስነው ጊዜ ሳይገድበውዘመን ሳይቆጠርለት ዓለምን ከመፍጠሩ በፊት የነበረ ዓለምንም ፈጥሮ ያለ ዓለምንም አሳልፎ የሚኖር አምላክ ነው፡፡ ምነው ሰማየ ሰማያት ለእግዚአብሔር ይላልሳ መዝ.113÷24 ምድርን ለቀው በሰማይ ይኖራሉ ለማለት ነውን? ቢሉ ሰማይ ከፋ ያለ ልዑል ነው ሥላሴም ልዑላነ ባሕርይ ናቸውና ልዕልናቸውን መናገር ነው እንጂ ሥላሴስ በዓለሙ ኹሉ ምሉዓን ናቸው፡፡ 'በእንተ ዕበየ ልዕልናከትትሜሰል በደመናት - ደመና ከፍ ብሎ እንዲታይ ስለ ልዕልናህ ለደመና ትመሰላለህ'እናደን ኣትናቴዎስ፡፡ በሥላሴ መውጣት መውረድ መቆም መቀመጥ የለባቸውም፡፡ ከምድር የወደቀውን ያነሣ ዘንድራሱን ዘንበል ማድረግ ጎንበስ ቀና ማለት የለበትም ኹሉ በእጁ የተያዘ ነው እንጂ እንደለ ኣባ ሕርያቆስቅን ልቦና ላላቸው ሰዎች እግዚአብሔር የቀረበ ነው፡፡ ቅረቡ ኅቤሁ ወያበርህ ለክሙ ወደሱ ቅረቡ እሱያበራላችኃል ይላልሳ ክቡር ዳዊት መዝ. 33 ÷ 5 ቢሉ ረድኤቱን ስለሰጠን እግዚአብሔር ቀርበን ረድኤቱን ስለነሣን እግዚአብሔር ራቀን እንደማለት ነው፡፡
ሰውም ኃጢአት ሠርቶ በግብሩ ይለያል እንጂ የሥላሴ ሥልጣን በሁሉ ምሉዕ ነው፡፡ ከአድማስ በላይ ከበርባኖስ በታች ወሰን መጨረሻ የላቸውምና ለስልጣናቸውም የተለየ ቦታ የለውም፡፡ ከላይ ጠፈር ከታች መሠረት የለውም ጠፈሩም መሠረቱም እሱ ነው እንጂ እንደለ ኣባ ሕርያቆስ መላእክትም ፈጣሪያቸው ለተልእኮ በጠራቸው ጊዜ ወደ ላይ እስከ ጽርሐ ኣርያም ወደታች እስከ በርባኖስ እንደ ቅጽበተ ዓይን ይደርሳሉ በዚህ ፍጥነታቸው እልፍ አዕላፍ ዘመን ሲበሩ ቢኖሩ ሥላሴ የሌለበትን ቦታ አያገኙም፡፡ይኽን ብላ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ቅዱሳን መጽሓፍትን አስረጂነት በማድረግ ስታስተምረን የማይመረመሩ መኾናቸውንም ስታስተምር እንዲኽ ብላ ትመክራለች÷
ጥንት ሰው ሲወለድ ለልማዱ አባት ሲቀድም ልጅ ሲከተል ነው ÷ይኽ ግን ዕፁብ ድንቅ እንዲህ ነው ተብሎ የማይነገር ከሕሊና ኹሉ ከፍ ያለ የማይመረመር ነው፡፡' ልደተ ወልድ ወፀዐተ መንፈስ ቅዱስ እምኣብ ይትነከር ወኢይትነገር ወይትሌዓል እምኩሉ ሕሊና ወኢይትረከብ- የወልድ ከኣብ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጽ ዕፁብ ድንቅ ይባላል እንጂ እንዲህ ነው ተብሎ ሊነገር ሊመረመር አይችልም ከኹሉ በላይ ስለኾነ አርቀውም ቢመለከቱ አይገኝም' እንዳለ ዲዩናስዮስ
የወልድ ከአብ መወለዱ የመንፈስ ቅዱስ መሥረፁ እንደምን ነው ቢሉ÷ቃልና እስትንፋስ ልብ ሳይቀድማቸው አካላቸው ከልብ ሳይለይ ቃል እንዲገኝ እስትንፋስ እንዲወጣ ወልድና መንፈስ ቅዱስም ቅድመ ዓለም አብ ሳይቀድማቸው እንበለ ተድኀሮ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ አካል ዘእምአካል÷ወልድ ተወልደ÷መንፈስ ቅዱስ ሠረፀ፡፡ ከመቃል ወፀዓተ እስትንፋስ እምልብ ከማኹ ልደቱ ለወልድ ወፀዓቱ ለመንፈስ ቅዱስ- ቃል እስትንፋስ ከልብ እንዲወጡ የወልድ ከኣብ መወለድ የመንፈስ ቅዱስም ከኣብ መሥረጽ እንደዚያው ነው እንዳለ ርቱዓ ሃይማኖት ልብ ቃልን ይወልዳል ለልብና ለቃል ግን ሕይወታቸው መንፈስ ቅዱስ ነው እንዳለ ሳዊሮስ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ስለመስረጹ 'እኔከአብ ዘንድ የምልክላችሁ ጰራቅሊጦስ እርሱም ከኣብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለእኔ ይመሰክራል' ከአብ የሰረፀ መንፈስቅዱስ ምስክሬ ነው ብሏልና፡፡ ዮሐ.15÷26. ዮሐ. 16÷28 በማለት የማይመረመር መኾኑን ቅዱሳን አባቶች ያስተማሩትን ትምሕርት ዛሬም ቤተክርስቲያናችን ይኽንኑ ትምሕርት አጽንኦት በመስጠት ትመሰክራለች ታስተምራለች፡፡
የሥላሴ ግብራቸውንም በተመለከተ- ግብራቸውና ስማቸው አይፋለስም በማለት ይሕችው'ግንቡ ንፁህ መሰረት ደም ነው'የተባለላት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ስታስተምር የወልድ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ መሥረፅ ከአብ መውጣት ነውን? ቢሉ አዎን፡፡ የኹለቱም መውጣት ከኾነ ወልድን ሠረፀ መንፈስ ቅዱስን ተወለደ ያሉ እንደኾነ አይገባምን? እንደምን ነው ቢሉእነኾ ከልብ ቃልና እስትንፋስ ይወጣሉ መውጣት ስላስተባበራቸው ቃልን ተነፈሰ እስትንፋስን ተናገረ እንደማይባል ወልድን ሠረፀ መንፈስ ቅዱስ ተወለደ ማለት አይገባም፡፡
ከላይ ግብራቸውና ስማቸው አይፋሰስም እንደተባለ ኹሉ ስማቸውና አካላቸው እንደማይቀዳደሙ ይኽውም ንጽሕት ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ስትመሰክር- ስም አካል ቀድሞት እንደሰው ስም በኃላ የተገኘ አይደለም÷የሰው ግን ስሙን አካሉ ቀድሞት በኃላ ይገኛል ፤ ወንዱን በአርባ ቀን ዕገሌ ይሉታል፤ ሴቲቱን በሰማንያ ቀን ዕገሊት ይሏታል ፤ የተወለደውም ዕለት እናት አባቱ ዓለማዊ ስም ያወጡለታል እንደዚኽ አይደለም፡፡ ከአካሉ አካሉ ከስሙ ሳይቀድም እንደተገኘ የሥላሴም ስማቸው ከአካላቸው አካላቸው ከስማቸው ሳይቀድም ቅድመ ዓለም የነበረ ነው እንጂ ድኅረ ዘመን የተገኘ አይደለም፡፡ 'ሥላሴ ከአካላቸውና ከስማቸው አንዱ ለአንዱ ደቂቃ ስንኳን ወደኃላ የተገኘ አይደለም፤ ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር ባንድነት የነበረ ነው እንጂ' እንዳለ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት
በስም ሦስት እንደኾኑ በኣካልም ሦስት ናቸው፡፡ ለአብ ፈጽሞ አካል አለው፡፡ለወልድም ፈጽሞ አካል አለው፡፡ ለመንፈስ ቅዱስም ፈጽሞ አካል አለው፡፡ አካሉ ግን የማይመረመር ምሉዕ ስፍሕ ረቂቅ ነው፡፡ እርሱ ራሱ ቢያውቀው እንጂ ሌላ ኣያውቀውም ፡፡ ፍጥረት ኹሉ በሱ ፊት በቅጠል ላይ እንዳረፈች ጠልና እንደወርቅ ሚዛን ማቅኛ ነው ብሎ ኢሳያስ በትንቢቱ ላይ እንደተናገረ፡፡ረቂቅም እንደኾኑ ኤጲፋንዮስ ስፋሕ ረቂቅ ብሏል፡፡ በስም ሦስት ብቻ ሳይኾኑ በገጽ ሦስት ናቸው ብላም በቅዱሳት መጽሓፍት አስረጂነት ቅድስት ቤተክርስቲያን እንዲ በማለት ትመሠክራለች- በአካል ሦስት እንደኾኑ በገጽም ሦስት ናቸው ለኣብ ፍጹም ገጽአለው፡፡ ለወልድም ፍጹም ገጽ አለው፡፡ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም ገጽ አለው፡፡ አይኹድና ሰባልዮስ ግን አንድ ገጽ ይላሉ፤ እንዲኽም ቢሉ፤'አዳም ኮነ ከመ አሐዱ እምኔነ- እነኾ አዳም ከኛ እንደ አንዱ ኾነ'አሉ ብሎ መጽሐፍ ይመሠክርላቸዋልና ይረታሉ፡፡ ዘፍ. 3÷22ለአብ ፍጹም መልክ አለው ለወልድም ፍጹም መልክ አለው ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም መልክ አለው፡፡ ለመለኮት ሦስት አካል ሦስት ገጽ ሦስት መልክ እንዳለው የተነገረው ኹሉ እናምናለን እንዳለ አትናቴዎስ አንዳንድ ሰዎች ግን ለሥላሴ መልክ የላቸውም ይላሉ፡፡ ምነው ቢሏቸው ኹሉን ሊያዩ ዓይን አላቸው ይላሉ÷ኹሉን ቢሰሙ ጆሮ አላቸው÷በምልዓት ኹነው ቢታዩ ገጽ አላቸው÷ በኹሉ ሊገኙ እግር አላቸው ÷ኹሉን ቢይዙ እጅ አላቸው ተባሉ እንጂ ይኽ ኹሉ የላቸውም ይላሉ እነሱ እንዲህ ቢሉ መጻሕፍት ይመሰክራልና ከሀዲዎች እንደሚሉት አይደለም፡፡
ራስ እንዳላቸው'ራሱንም እንደ ፀምር ነጭ ኹኖ አየኹት'ብሏል ራእ.1÷14
አፍንጫ እንዳላቸው 'የአቤልን መስዋዕት አሸተተ' ብሏል
አፍ እንዳላቸው'እግዚአብሔር ባፉ ጠርቶ ወዲህ ቅረብ አለኝ' ብሏል
ኢሳያስም እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረ ብሏል
ዓይን እንዳላቸው'የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ወዳጆቹ ነው'ብሏል መዝ.33÷15
ጆሮእንዳላቸው'ጆሮውም ወደ ልመናቸው ነው'ብሏል መዝ.33÷15
ፊት እንዳላቸው'የእግዚአብሔር ፊት ወደሚሠሩት ሰዎች ነው'ብሏል መዝ.33 ÷16
እግር እንዳላቸው'የጌታችን የአምላካችን የፈጣሪያችን እግር በቆመበት እንሰግዳለን'ብሏል መዝ.131÷7
እጅ እንዳላቸው'እጆችህም ፈጠሩን'ብሏል መዝ.118÷73
አባ ሕርያቆስም 'ለጴጥሮስ እንዳሳየው ኹሉ በእጁ የተያዘ ነው'ብሏል ኢሳያስም 'ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሮቼ መመላለሻ ናት'ብሏል ኢሳ.86 ÷1 ሐዋ. 7÷49 በዚኽ ኹሉ ሦስትነታቸው ታወቀ ተረዳ፡፡
የሥላሴ አንድነት በማን በማን ነው ቢሉ በመለኮት÷ በባሕርይ ÷በሕልውና÷በአገዛዝ ÷ በሥልጣን÷እንዲኽ በመሰለ ነገር ኹሉ አንድ ይባላሉ፡፡ አብ በተለያየ አካሉ ልብ ነው ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው አብ ነውና ሌላ ልብ የላቸውም፡፡ ልባዊያን መባላቸው በአብ ልብነት ነው፡፡ ወልድም በተለየ አካሉ ቃል ነው፡፡ ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ወልድ ነው ሌላ ቃል የላቸውም፡፡ ነባብያን መባላቸው በወልድ ቃልነት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም በተለየ አካሉ እስትንፋስ (ሕይወት) ነው ለኣብ ለወልድ ሕይወታቸው መንፈስ ቅዱስ ነው ሌላ ሕይወት የላቸውም ሕያዋን መባላቸው በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ነው፡፡
አብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው፡፡ ወልድም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው እንዳለ አቡሊድስ ሦስቱም በአብ ልብነት አስበው በወልድ ቃልነት ተናግረው በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ሕያዋን ሁነው ይኖራሉ፡፡ በአብ ልብነት በወልድ ቃልነት በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት እናምናለን እንዳለ ሳዊሮስ እንዴት አልኣዛርን ከሞት ያነሳው ኢየሱስ ነው ይባላል ጌታችንም እኮ ስለ ትንሣኤ ሙታን በተናገረው ትምሕርቱ 'በመቃብር ያሉ ኹሉ ቃሉን የሚሰሙበት ጊዜ ትመጣለችና ስለዚኽ አታድንቁ መልካም የሠሩም ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ የሠሩ ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ፡፡ እኔ ከራሴ አንዳች አድርግ ዘንድ አልችልም እንደሰማኹ እፈርዳለኹ እንጂ ፍርዴም እውነት ነው የላከኝን ፈቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና'በማለት ተራግሯል፡፡ ዮሐ. 5÷28-30 ትን. ዳን. 12÷2 የአልአዛርን በመቃብር አራት ቀን መተኛት እኅቱ ማርያም ጌታዬ ሆይ አራት ቀን ሆኖታልና ፈጽሞ ሸትቶ ይሆናል አላቸው፡፡ ይኽንንም ጌታ በሰማ ጊዜ ለማርታ የመለሰላት መልስ 'ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ አላልኩሽም ነበርን?' በማለት ነበር የመለሰላት፡፡ ይኽንንም ካለ በኃላ ዐይኖቹን አቅንቶ እንዲኽ አለ አባት ሆይ ሰምተኽኛልና አመሰግንሃለኹ፡፡ እኔም ዘወትር እንደምትሰማኝ አውቃለኹ ነገር ግን አንተ እንደላከኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ቆመው ሳሉ ሰዎች ይኽን እናገራለኹ በማለት ነበር የተናገረው ከዚኽም በኃላ ነው ክርስቶስ አልኣዛር ና ውጣ ብሎ ከሙታን ያስነሳው፡፡ ዮሐ 11÷1 -46 እዚህ ቃል ላይ ኹለት ነገሮችን ልብ ልንልና ልናስተውል ይገባል፡፡ አንደኛው ራሱ በአንደበቱ እኔ ከራሴ አንዳች አድርግ ዘንድ አልችልም------- የላከኝ ፍቃድ እንጂ የእኔን ፈቃድ አልሻምና በማለት የተናገረውንና አልአዛርን ከማስነሳቱ በፊት የለመነውን (የጸለየውን) ጸሎት ማስታወስ ይገባል፡፡ ለምን ቢባል ጌታ ራሱ በጸለየው ጸሎቱ ላይ አንደኛ ኣባት ሆይ ሰምተኽኛልና አመሰግንሃለሁ ያለውንና አንተ እንደላከኝ ያምኑ ዘንድ በማለት የተናገረውን ቃላት ማስተዋል ይገባል፡፡ ታዲያ በዚኽ ጌታ ራሱ በመሠከረው (ባስተማረው በጸለየው) ጸሎት በማን ፈቃድና ሥልጣን እንዳስነሳው በግልጽ የተቀመጠውን የመጽሓፍ ቅዱስ ቃልን ማጣመምና መቀላቀል መቀናነስና መጨማመር ስለምንስ አስፈለገ፡፡ ነገር ግን ለዮሓንስ ራዕይ ላይ 'ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር ከዚህ መጽሓፍ ውስጥ የተጻፈውን መቅሰፍት ይጨምርበታል፡፡ ማንም ከዚህ የትንቢት መጽሐፍ ቃል ቢያጎድል በዚህ መጽሓፍት ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እድሉን ያጎድልበታል' በማለት ተናግሯል፡፡ ዮሓ. ራእ 22 ÷18 -20 ስለዚህ አልአዛርን ከሞት ያስነሣው ኢየሱስ ብቻውን ነው ብለን ከማስተማራችን ከመመስከራችን በፊት ቆም ብለን በሚገባ ምሥጢረ ሥላሴን መማርና ማወቅ ይገባል ፡፡ እናውቃለን ብለን ራሳችንን የምናሳምን ከኾነ ግን ትምሕርታችን የክህደት ትምሕርት ስለኾነ ራሳችንን ልናገል ይገባል፡፡ ለኹላችንም እግዚአብሔር አምላክ ማስተዋልን ይስጠን ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ለዘለዓለሙ አሜን!
ኢዩኤል ሰሎሞን
ደብረ ብሥራት
ሐምሌ 26 ቀን 2003 ዓ.ም.
ምንጭ፡-
· አሥራው መጽሐፍ ቅዱስ
· ሃይማኖተ ኣበው
· ዓምደ ሃይማኖት
· የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት
· መንገደ ሰማይ
· ትምህርተ መለኮት
· የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አንቀፀ ብፁኣን ሰንበት ት/ቤት የኮርስ ማስተማሪያ መጽሐፍ፡፡
No comments:
Post a Comment