Thursday, March 22, 2012

የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ ፤ የምድርም ነገሥታት ኹሉ ይሰግዱለታል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

“የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ ፤ የምድርም ነገሥታት ኹሉ ይሰግዱለታል” መዝ.71÷10-11


እነኾ የጥበብ ሰዎች /ሰብአ ሰገል/ ከሩቅ ምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተልሔም አውራጃ መጡ፡፡ ከጥንት ዠምሮ በዓለም ሕዝብ መካከል ከዋክብትን የሚመረምሩ ጠቢባን ነበሩ፡፡ ትን.ዳን.1÷3 ስለነዚኽ ሦስት የሩቅ ምሥራቅ ነገሥታት አመጣጥ በስፋትና በጥልቀት በመዝ.71÷9-15 ኢሳ.60÷6 ኢሳ 49÷23፡፡ መመልከት ይቻላል፡፡

የጥበብ ሰዎች ስማቸው በድርሳነ ማርያም ላይ ተገልጧል፡፡ ታኔሱራም፣መሊክ፣ ዲሰስባ ወይም በትርጓሜ ወንጌል ላይ እንደተገለጸልን ማንቲሱራ፣መሊኩ፣በዲዳዝፋር በማለት ይጠራቸዋል፡፡

ከምሥራቅ የተነሡት ሰብአ ሰገል በምሥራቅ በኩል ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር፡፡ ለልማዱ ከሰው ሊደርሱ ይሰወራቸው ከሰው ሲለዩ ይመራቸው ነበር፡፡ መርቶ ከየት ያደርሰን ይኾን ብለው ኹለት ዓመት የተከተሉት ኮከብ ካሰቡት ቢያደርሳቸው ሕፃኑን አይተው ፈጽመው ደስ አላቸው፡፡ ምሥራቅ እመቤታችን ስትኾን ኮከብ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በትንቢትም ከያዕቆብ ይወጣል የተባለ ኮከብ እርሱ ነው፡፡ ዘኁ. 24 ÷17 እርሱም የሚያበራ የንጋት ኮከብ ነኝ ብሏል፡፡ ራእ.22÷16 ነገሥታቱም በኮከብ ተመርተው ቤቱን /የከብቶቹን ግርግም/ ባገኙ ሰዓት ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ባዩዎቸው ጊዜ በጣም ደስ አላቸው ሳጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ ፣ ዕጣንና ከርቤን አቀረቡለት፡፡


ወርቁ ምሳሌነቱ

ከአኹን ቀደም ወርቅ የሚገበርላቸው ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው፡፡ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርኽ ኋላም የማታልፍ ዘላለማዊ ንጉሥ ነኽ ወርቅ ንጽሕ ነው አንተም ንጹሕ ባሕርይ ነኽ ሲሉ ነው፡፡ ወርቅ ከዚኽ ሌላ ሃይማኖትን ከምግባር ለሚያስተባብሩ ምእመናን፣ በእሳት ለሚፈተኑ ሰማዕታት፣ቀጥተኛ ለኾነ ሃይማኖት እንዲኹም ለቅዱሳን መላእክት ምሳሌ ነው፡፡

ዕጣኑ ምሳሌነቱ

ከኣኹን ቀደም የምናጥናቸው ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው፡፡ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርኽ ኋላም የማታልፍ የዘላለም ካህን ነኽ ሲሉ ነው፡፡ ዕጣን ምዑዝ ነው፡፡ አንተም ምዑዘ ባሕርይ ነኽ ሲሉ ነው፡፡ በተጨማሪም በአንተ ያመኑ ምዕመናን ምዑዛነ ምግባረ ወሃይማኖት ናቸው፡፡ ዕጣን የባሕታውያን ምሳሌ ነው፡፡ ዕጣን ከሩቅ እንዲሸት ተስፋም ያልያዙትን እንደያዙት ያላዩትን እንዳዩት ታደርጋለችና፡፡ ክርስቶስም እመቤታችንም በዕጣን ይመስላሉ፡፡

ከርቤ ምሳሌነቱ

አንተ ቀድሞም ያልተፈጠርኽ ኋላም የማታልፍ ብትኾንም በሰውነትኽ መራራ ሞትን መቀበል አለብኽ ሲሉ ነው፡፡ ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል፡፡ የተለየውን አንድ ያደርጋል፡፡ አንተም ከማኀበረ መላእክት የተለየውን አዳምን መልሰኽ አንድ ታደርገዋለኽ፡፡ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተኽ ታጸናዋለኽ ሲሉ ነው፡፡ አንድም በዕለተ ዓርብ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት፡፡ ከርቤ የምዕመናን ምሳሌ ነው፡፡ ምክንያቱም በፍቅር አንድ ኾነው የሚኖሩ ናቸውና ፡፡

ይኸ ኹሉ የኾነው ከሰው አእምሮ በላይ በኾነ በእግዚአብሔር ጥበብ ነው ፡፡ ወርቅ ያመጣ የሴም ወገን ነው፡፡ መንግሥት ከነገደ ሴም ነውና፡፡ ዕጣን ያመጣው የያፌት ወገን ነው፡፡ ከነገደ ያፌት ካህናት ይበዛሉና፡፡ ከርቤ ያመጣ የካም ወገን ነው፡፡ ምዕመናን ከነገደ ካም ይበዛሉና፡፡ የተገበረው ወርቅ ዕጣንና ከርቤ ከየት መጣ ለሚለው፡፡ ቀድሞ ቅዱስ ሚካኤል ፣ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስ ሩፋኤል ለአዳም ሰጥተውታል፡፡ አዳም ደግሞ ለሔዋን ሰጣት፡፡ ይኽም በጥበበ እግዚአብሔር ሲወርድ ሲዋረድ ከልደተ ክርስቶስ ደርሷል፡፡

የስብአ ሰገል ስጦታ ወርቅ ዕጣን ከርቤ ነበር፡፡ የእኛ ስጦታስ ምን ይኾን? ሰብአ ሰገል እነዚኽን ስጦታ ለአምላክ አቅርበው ወደ መጡበት ተመልሰዋል እኛስ ወደቅድስ ቤተክርስቲያን ኄደን /ተሰባስበን / ምን ሰጥተን ይኾን የምንመልሰው ሕይወታችንን ፣ ራሳችንን ፣ ልባችንን፣ ንጽሕናችንን ፣ ምስጋናችንን ወይስ? …….ራሳችንን በጥልቀን ልንመረምርና ልንፈትሽ ይገባናል፡፡

ምንጭ - ሰማንያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ 2000ዓ.ም ሕትመት፣ ድርሳነ ማርያም፣ ትርጓሜ ወንጌል ዘማቴዎስ፣ወላዲተ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ፣የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ /አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ/ቀ/ዶ/ምክረ ሥላሴ አንደኛ መጽሐፍ ፣የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት

ይትባረክ እግዚአብሔር ኣምላከ አበዊነ

ኢዮኤል ሰሎሞን /ደብረ ብሥራት/
ታኀሣሥ 2004ዓ.ም

No comments:

Post a Comment