Thursday, March 22, 2012

ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኀጢአት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኀጢአት - ኀጢአትን ለማስተሰረይ በምንጠመቃት በአንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡ 
ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምእት

እንደ ናዝራውያን ሥርዓት በሦስትነት በምናመሰግነው እንደ ሱራፌልም ቃል በምናመሰግነው የሰው እጅ በማይነካው የሟችም ኀሊና በማይመረምረው በጽርሐ አርያም አትሮንሱን ያኖረ በተራሮች ራስ ላይ የጉምንተን በሚያተን ያለጩኸት የሚያስወግደው በአየራት ውስጥ በሚያመላልሰው ሰፊውን የሰማይ ገጽ የደመና ግምጃን በሚያላብሰው በእግዚአብሔር ስም ክብርና መመስገን የሚገባው ለዘላለሙ አሜን፡-

ጥምቀት ማለት በምስጢረ ሥላሴና በምስጢረ ሥጋዌ ለሚያምን ሰው ኹሉ የተሰጠ የኃጢአት መደምሰሻና ከእግዚአብሔር የጸጋ ልደትን መቀበየ ነው፡፡ ጥምቀት የኃጢአት መደምሰሻ እንደሚኾንም እግዚአብሔር አስቀድሞ በነቢያት ትንቢት አናግሮ ትንቢቱም በትንቢተ ሕዝቅኤል ላይ ……. የጠራ ውሃ አፈስባችኋለሁ ትጠሩማለችሁ ከርኩሰታችሁም ሁሉ አነጻችኋለሁ፡፡ በማለት ተናግሯል፡፡ ሕዝ . 36÷25 በመቀጠልም መልሶ ይምረናልኃጢአታችንንም ያጠፋል ኃጢአታቸው ኹሉ ወደ ጥልቅ ባሕር ትጥላለኽ ማለት ኃጢአታቸውን በጥምቀ ታስተሰርያለህ……./ትደመስሳለህ/ ሚክ. 7÷19

ጌታም እውነት እውነት እልኻለሁ ማንም ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ይገባ ዘንድ አይችልም፡፡ ዮሐ.3÷5 እንግዲህ ኂዱና አሕዛብን ኹሉ አስተምሩ አጥምቋቸውም በአብና በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ፤ ማቴ. 28÷19 ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል፡፡ ማር.16÷16 ተብሎ ተጽፏል፡፡

ከእግዚአብሔር መወለዳችን የእግዚአብሔርን ርስት መንግሥት ሰማይን ለመውረስ ነው ፤ መንግሥት ሰማይንም በጥምቀት ልንገባባት እንደምንችል ጌታችን በዚኽ ትምህርቱ እንደገለጸልን አውቀን መኖር ይገባናል፡፡ ይኽም የጌታ ትምህርት ስለጥምቀት ለነቢያት ትንቢት መፈጸሚያ ለሐዋርያት ትምህርት መምሪያ ነው፡፡ ምነው ጌታ ፈጣሪ እግዚእ ሲሆን ወደ ትሑት ዮሐንስ ኄደ ቢሉ ሥጋ መልበሱ ለትሕትና ነውና፡፡ በዚያውም ላይ ነገሥታት መኳንንት ቀሳውስትን መጥታችሁ አጥምቁን አቁርቡን ባሉ ነበርና፤ እኔ የሰማይ የምድርም ንጉሥ ስሆን ÷ኄጄ ተጠምቄ ያለሁና እናንተም ኂዳችሁ በቀሳውስት እጅ ተጠመቁ ቁረቡ ሲል ነው፡፡ ጌታ መጠመቁ ብዙ ምስጢር አለው፡፡ መጀመሪያው ምክንያት አቤቱ ውኖች ዓዩኽ ተጨነቁም ቀላዬችም ተንቀጠቀጡ ተብሎ ትንቢት ተነግሮለት ነበር ይኽን ትንቢት ለመፈጸም ተጠመቀ፡፡ መዝ. 77÷16 እንደ ትንቢቱም ቃል ጌታ ሊጠመቅ በገባበት ግዜ የዬርዳኖስ ውሃ ከመካከሉ ተከፍሎ ወደ ኋላው ሸሽቷል እሳትም እንዳነደዱበት ሁኖ ፈልቷል፡፡ ፈልሑ ማያት ዲበ ርእሱ - ውኖች በራሱ ላይ ፈሉ እንዳለ ቅዱስ ያሬድ

የዬሐንስንም ምስክርነት ለማስረዳት ነው፡፡ ዮሐንስ ከእኔ በፊት የነበረ ከእኔ የሚበልጥ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤ ብሎ በቃል መስክሮለት ነበረና ለሕዝቡ ተገልጾ እንዲታይ እንዲታወቅ ነው፡፡ ይኽም ሊታወቅ የተገለጠበት ዕለት ኤጲፋንያ ተብሏል፡፡ ኤጲፋንያ የፅርዕ /የግሪክ/ ቋንቋ /ቃል/ ሊኾን በግእዝ አስተርእዬ ተብሏል፡፡ በዐማርኛ መታየት መገለጽ ማለት ነው፡፡ መጠመቁን የፈቀደበት ምክንያት ሲገልጽ ግን በጥምቀቱ ውኖችን ሊቀድስልን አምናችሁ ብትጠመቁ ከኃጢአት መንጻትን ከመንፈስ ቅዱስ ልደትን ታገኛላችሁ ብሎ ሲያስተምረን ነው፡፡ ሃይ. አበ. ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ፡፡ ኀጢአት ኑሮበት ንጹሕ ሊኾን የተጠመቀ አይደለም በንጹሕ ከሱ ጋራ አንድነትን ይሰጠን ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ……ሃይ. አበ. ዘጎርጎርዮስ

ኹሉን ማድረግ የሚችል ጌታ በማር በወተት ያልተጠመቀ በውሃ የተጠመቀ ሰለምን ነው ቢሉ ማር ወተት ለባለጸጋ እንጂ ለደሀ አይገኝምና ጥምቀትን ለሁሉ በሚገኝ በውሃ አድርጎ እንደሰጠን ሊያጠይቅ ነው፡፡ ዳግመኛ ማር ወተት ለተክል ቢያጠጧቸው ቢያደርቁ እንጂ አያለመልሙም÷ውሃ ግን ያለመልማልና በውሃ ብትጠመቁ ልምላሜ ነፍስ ታገኛላችሁ ሲል ነው፡፡ ማር ወተት መልክአ ገጽ አያሳዩም ÷ውሃ ግን መልክአ ገጽ ያሳያልና በውሃ ብትጠመቁ መልክአ ሥላሴ ይሳልባችኋል ሲል ነው ማር ወተት ልብስ ያሳድፋል እንጂ አያነጻም÷ ውሃ ግን ያነጻልና በውሃ ብትጠመቁ ንጽሐ ነፍስ ታገኛላችሁ ሲል ነው፡፡ ዳግመኛም ውሃ ካለበት ዘንድ ተሐዋስያን አያገኙም ማር ወተት ባሉበት ግን ተሐዋስያን አይለዩምና አጋንንትም ወደ ጥሙቀን እንዳይቀርቡ ከኢጥሙቃን እንዳይለዩ ሲያጠይቅ ነው፡፡ ዳግመኛም ማር ወተት ቢፈሱ ከቅርብ ይቀራሉ እንጂ ከሩቅ አይደርሱም፡፡ ውሃ ግን እሩቅ ይደርሳልና ጥምቀትም ጽንፍ እስከ ጽንፍ እንደደረሰ ለማጠየቅ ነው፡፡ ዳግመኛም ዳዊት ርእዩከ ማያት እግዚአ ርእዩከ ማያት ወፈርሑ- አቤቱ ማየት ዓዩህ አይተውህም ሸሹ ያለው ትንቢት እንደ ደረሰ እንደ ተፈጸመ ለማጠየቅ ነው፡፡ መዝ. 76÷16 ፈርኦንን ከነሠራዊቱ በውሃ አጥፍቶት ነበርና ዲያብሎስንም ከነሠራዊቱ በጥምቀት ለማጥፋት ነው በፈርኦንም አድሮ የነበረ ሰይጣን በዚያው በኩል ወደ ሲኦል እንደ ወረደ በቁራኝነትም የነበሩ አጋንንት በጥምቀት ድል ይነሣሉ ሲል ነው፡፡ በዕለተ ኀሙስ ለታውጽእ ባሕር ባለ ጊዜ በደመ ነፍስ ሕያዋን የሚኾኑ ፍጥረታት ተገኝተዋል ከነዚኹም በዚያው ጸንተው የሚኖሩ ወጥተው የኄዱ ÷አንድ ጊዜ ከባሕር ጸንተው የሚኖሩ አሉ ዘፍ.1÷10 ዘጾ.14 ÷26-31

ዮሐንስም ሎሌ ከጌታው ይኄዳል እንጂ ጌታ ከሎሌው ሊጠመቅ ይኄዳልን? እንደዚኹስ ኹሉ እኔ ካንተ ዘንድ ለመጠመቅ እመጣለኹ እንጂ ÷አንተ ከኔ ዘንድ ለመጠመቅ ትመጣለኽን? ብሎ አይኾንም አለው፡፡ ኀድግ ምዕረሰ አንድ ግዜስ ተው አለው አንድ ጊዜስ ተው ማለቱ ጌታ ሲጠመቅ ዮሐንሰ ሲያጠምቅ አይኖርምና፡፡ እስመ ከመዝ ተድላ ለነ÷ይኽ ለኛ ተድላ ደስታችን ነውና÷አንተ እኔን አጥምቀኽ መጥምቀ መለኮት እየተባልኽ ልዕልናኽ ሲነገር ይኖራል፡፡ እኔም ባንተ እጅ ተጠምቄ በባሪያው እጅ ተጠመቀ እየተባለ ትሕትናዬ ሲነገር ይኖራልና ይኽ ለእኛ ተድላ ደስታችን ነው፡፡ ማቴ. 3÷15 መዝ. 110÷4 ዮሐንስም ሌላውን በአንተ ስምከ አጠምቃለሁ አንተን ምን እያልኩ አጠምቅሃለሁ አለው፡፡ ጌታም ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ፡፡ የብርሃን የዕውቀት ባለቤት የወንጌል መምህር የአብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር በለን፡፡ ነዋ በግፁ ለእግዚአብሔር ዘየ አትት ኃጢአተ ዓለም ፡፡

የዓለሙን ኃጢአት ለማስተሥረይ የመጣ የእግዚአበሔር መሥዋዕቱ እነኾ እያልክ አጥቀኝ አለው ዩሐ. 1÷30 ይኽን ተባብለው ኹለቱ እጅለእጅ ተያይዘው ወደ ባሕሩ ገቡ÷በዚኽ ጊዜ እጁን አልጫነበትም ከራሱ ላይ ረቦቆም ወፈልሑ ማየት ከመዘእምአፍላግ እንዲል ፤ ውሃው እየተመላለሰ ሦስት ጊዜ አልብሶት ወረደ ÷እጁን ከራሱ ላይ ረቦ መቶሙ ስለምን ነው ቢሉ ሊቀ ከህናታችሁ ይኽ ነው የቀድሞ መሥዋዕታችሁ አለፈ ፤ እንግዲኽ ወዲኽ መሥዋዕታችሁ ይኽ ነው ብሎ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያለ ነው፡፡ መጠመቁም ለኛ አብነት ለመኾን ÷ጥምቀትን ብርህት ጽድልት ለማድረግ ለጥምቀት ኃይልለመስጠት ነው፡፡ እኛም ኃይል መንፈሳዊ በየጊዜው እንዲጨመርልን እሱን አብነት አድርገን እንጠመቃለን፡፡

የአንድነትና የሦስትነት መገለጥ እንዴት ነበር

ጌታ ተጠምቆ ከውሃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱሰ በርግብ አምሳለ ወርዶ ከራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ አወራረዱ እንደምን ነው ቢሉ አነድ ክነፍን ወደ ሰማይ ÷ አነድ ክንፍ ን ወደ ምድር አድርጎ ወርደል የአብ ሕይወት የወለድ ሕይወት ነኝ ሲል በርግብ አምሳልመውረዱ ሰለምን ነው ቢሉ÷ ርግብ የዋህ ናት÷ መንፈስ ቅዱስም በየዋሃን ሰዎች ያድራልና ፡፡ ርግብ በኖኀ ጊዜ ኀፀ ማየ አይህ ነትገ ማየ አይሕ ስትለ ቆጽለ ዕፀዘፍትን ይዛ ተገኝታለች፡፡ /ዘፍ.8÷8-12/

መንፈስ ቅዱስም ሐፀ ማየ ኃጢአተ ነትገ ማየ መርገም አያለ ተስፍ መስቀል ያበሥራልና፡፡ ወይንሣእ መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ- መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ/ማቴ. 16÷24/፡፡ ስለዚኽ ነገር በርግበ አምሳል ወረዶ አማናዊ ርግብ አለመኾኑ በምን ይታወቃል ? ቢሉ ÷ ጌታ የተጠመቀ በአሥረኛው ሰዓት ሌሊት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ተሕዋስያን ከቦታቸዉ አይናወጹምና በዚኽ ታዉቋል፡፡ በዚኽ ጊዜ አበ በደመና ሁኖ ዝንቱውአቱ ወለድየ ዘአፈቅር- ለመሥወዕት የፈቀድሁት በርሱ ህለው ሁኜ የምመለክበት የምሰገድለት ልጄ ይኽ ነው አለ፡፡ /ማቴ.3÷17/፡፡ አንድ አካልአንድ ባሕርይ አድርጎ ዝንቱ ይኽ ልጄ ነው አለ÷ ኢይቤ ዘላዕል ዝንቱ ወልድየ አላ ይቤ ዝንቱ ወዕቱ ወልድየ -በዚኽ አድሮ ያለ ልጄ ነው አላለምአንድ አካል አንድ ባሕሪይ አርጎ ይህ ልጄ ነው አለ÷ እንጂ እንዳለ ቄርሎስ የአብ ምስክርነት የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ከውሃው ከወጣ በኋላ ነው ፡፡ ወልድ በክበብ ትስብዕት በጽንፈ ዩርዳኖስ ቁሞ ሲታይ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ከራሱ ላይ ሲቀመጥ÷ አብ በአየር ኹኖ ሲመስክር ÷ የአንድነት የሦስትነት መሰጢር ተገለጠ፡፡ ይኽ የአንድነትና የሦስት ምስጢር በምስጢረ ሥላሴ አስተምሮ ላይ ርቀታቸውን ሲገልጽ ሥላሴ በአካል ሦስት ናቸው፤ ለሥልጣናቸውም ወሰን መጨረሻ የለውም ካልን፤ ሰው አብሮ በተቀመጠ ጊዜ ፈቅ በልልኝ አታስጨንቀኝ ብሎ ይከላከላል፤በሥላሴ እንዴት ነው ቢሉ? ሰው ግዙፍ ነውና ይከላከል፤ ሥላሴ ግን ረቂቃን ናቸውና አይከላከሉም፡፡ መከላከልስ እንደሌለባቸው ምሳሌ ያስረዳል፤ በመዓልት ብርሃንና ሙቀት ነፋስ ሦስት ፍጥረታት መልተው ይውላሉ፤ ብርሃኑ ሲኄድ ሲሠራበት ይውላል ፡፡ ሙቀትንና ረፋስን ፈቅ በሉልኝ አይላቸውም፡፡ ነፋስም ዛፍን ሲያናውጽ ይውላል ሙቀትንና ብርሃንን ፈቅ በሉልኝ አይላቸውም፡፡ ሙቀትም የበረደውን ሲያሞቅ የረጠበውን ሲያደርቅ ይውላል፤ብርሃንና ነፋስን ፈቅ በሉለኝ አይላቸውም፡፡ እሊህስ እንኳን ረቂቃን ነን ብለው አይከላከሉም፡፡ ከእሊህ ይልቅ ሥላሴ ይረቃሉና መከላከል የለባቸውም፡፡

ከኹሉም መላእክት ይረቃሉ ከአካላቸወም ርቀት የሕሊናቸው ርቀት ይበልጣል÷ ይኽ የሕሊናቸው ርቀት በሥላሴ አካል ርቀት አንጻር እንደተራራ ገዝፎ ይታያል፡፡ ቅጥነተሕሊናሆሙ ለመንፈሳውያን በኀበ ቅጥነቱ ከመ እንተ ሥጋ ገዚፍ- በሥላሴ ርቀት የመንፈሳውያን መላእክት ርቀት አደን ግዙፍ ሥጋ ነው፡፡ እንዳለ አረጋዉ መንፈሳዊ፡፡ በዚኽም በዕለተ ጥምቀት ሥስትነታቸው በግልጽ የታየበትና የተገለጸበት ዕለት ነው፡፡ አብ በደመና ውስጥ ወልድ ሥጋንና መላኮትን አዋሕዶ በመጥምቁ ዩሐንስ አጠገብ በመቆም መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወደ ምድር/በወልድ/ላይበማረፍ ታየቷዋል፡፡ በዚኽ ዕለትም የሥላሴ በአካል ሦስት መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ በአካል ሦስትነታቸውም እንዴት ነው ? ቢሉ በስም ሦስት እንደኾኑ በአካልም ሦስት ናቸው፡፡ ለአብ ፍጹም አካል አለው፡፡ ለወልድ ፍጹም አካል አለው ፡፡ለመንፈስ ቅድስም ፍጹም አካል አለው፡፡ አካሉ ግን የማይመረመር ምሉዕ ስፍሕ ረቂቅ ነው፡፡ እርሱ ራሱ ቢያውቀው እንጂ ሌላ አያውቅም፡፡ ኩሉ ፍጥረት ወኩሉ አሕዛብ ከመ ነጥበ ጠል ወከመ ለጽሊጸ ልሳነ መዳልው በቅድሜሁ- ፍጥረት ሁሉ በሱፊት በቅጠል ላይ እንዳረፈች ጠልና እንደ ወርቅ ሚዛን ማቅኛ ነው ብሎ ኢሳያስእንደተናገረ፡፡ ታዲያ ሦስት ናቸው ስንል አንድነታቸውስ በምን በምን? ነው ቢሉ ፡- በመለኮት ÷በባሕርይ ÷በህልውና ÷በአገዛዝ÷ በሥልጣት÷በመፍጠር÷በእግዚአብሔርነት÷በከሐሊነት÷በአምላክነት÷በብርሃንነት÷በጌትነት÷በአለመለወጥነት÷በአለመከፋፈልነት÷በእውቀትነት ÷በጥበብነት÷በቸርነት÷በፍቅርነት ÷በጽድቅነት÷በታማኝነት÷በምርጫነት÷በውሳኔነት ÷በመጋቢነቱ …… እንዲህ በመሰለ ነገር ኹሉ አንድ ይባላሉ፡፡ በዕለተ ጥምቀት በሶስትነት መታየታቸው ግን ፡- አብ በተለየ አካሉ ልብ ነው ፤ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው አብ ነው፡፡ ሌላ ልብ የላቸውም፡፡ ለባውያን መባላቸው በአብ ልብነት ነው፡፡ ወልድም በተለየ አካሉ ቃል ነው፤ ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ወልድ ነው፤ ሌላ ቃል የላቸውም፡፡ ነባብያን መባላቸው በወልድ ቃልነት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በተለየ አካሉ እስትንፋስ /ሕይወት /ነው ለአብ ለወልድ ሕይወታቸው መንፈስ ቅዱስ ነው ሌላ ሕይወት የላቸውም ሕያዋን መባላቸው በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ነው፡፡

አብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው፡፡ ወልድም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው፡፡ እንዳለ አቡሊድስ ሦስቱም በአብ ልብነት አስበው በወልድ ቃልነት ተናግረው በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ሕያዋን ሁነው ይኖራሉ፡፡ በአብ ልብነት በወልድ ቃልነት በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት እናምናለን እንዳለ ሳዊሮስ አብ በሰማይ ወልድ በምድር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ሆኖ ሶስትነት ይገለጽ እንጂ በሶስትነት አንድነት በአንድነት ሶስትነት አለ ብለን እናምናለን፡፡ ኽም እንዳለና እንዲታወቅ በምስጢረ ጥምቀት ዕለት ተገልጾልናል፡፡

ስለ ጥምቀት ታሪክና ምስጢር በብሉይ ኪዳን

አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰይሞ ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎምርን ወግቶ ድል ነሥቶ ሲመለስ ኃይል ቢሰማው÷ልጅኀን ከሰማየ ሰማያት ይወርዳል ከድንግል ማርያም ይወለዳል ብለህ ነበር÷ከዚኽ ዘመን ደርሼ፤ የቃሉን ትምህርት የእጅን ታምራት አያለሁን? ይቀርብኛል ብሎ ጸለየ፡፡ ከጌታም ከማረከው ከአሥር አንዱን ይዘኽ ዬርዳኖስን ተሻግረኽ ከመልከጼዴቅ ዘንድ ድረስና አምሳሉን ታያለህ እንጂ ከዘመኑስ አትደርስም አለው፡፡ መልከ ጼዴቅንም አብርሃም ይመጣልሃልና ኀብስተ አኮቴትን፤ ጽዋዓ በረከትን ሰጠው አለው መልከ ጼዴቅም ቡሩኩ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር÷የእግዚአብሔር ወዳጅ ብሎ ሰጠው ዘፍ 1417-18፡፡ አብርሃም ኀብስቱንም በልቶ ወይኑን ጠጥቶ ፤ ከአሥር አንዱን ሰጠው፡- ዬርዳኖስ የጥምቀት፤ አብርሃምየምሃዐመናን፤ መልከ ጼዴቅ የካህናት ፤ ኀብስተ አኰቴቅ ጽዋዓ በረከት የሥጋው የደሙ አምሳል ነው÷አብርሃም ዬርዳኖስን ባይሻገር መልከ ጼዴቅን ባለወቀውም ነበር ምዕመናንም ባይጠመቁ ሥልጣነ ክህነትም ባላወቁ ነበር ና ሥልጣነ ክህነትን ለማሳወቅ በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡


አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ባይኄድ መልከ ጼዴቅን ባላወቀውም ነበር፡፡ እንዳለ ቄርሎስ

ኢዬብም ደዌ ሥጋ ታም ሳለ÷ ከጌታዬ ከፈጣሪዬ የሚያወቃቅሰኝ ጽኑ ዳኛ ÷የውል ሽማግሌ አይገኝም እንጂ ባይገኝስ በጥሬ ዱቄት ባንድ ኹለት በተከፈልኹት ነበር አለ ጌታም ከአምላክ መዋቀስ÷ ትችላለህን? መወቃቀስስ ይቅርና ምድርን በምን ላይ ዘርግቻታለሁ ፤ አቁሜያታለሁ መጠኗስ ምን ያህል ነው ቢለው አቤቱ እንዲህማ ካልከኝ አፌን በእጄ እይዛለሁ እንጂ አለው ፡፡ ኢዮብ 38 ÷4 ተሰዓሎ እግዚአብሔር በደመና ወበዓውሎ ….. ጌታም የኢዮብን ትሕትና ዓይቶ በዮርዳኖስ ታጠብ አለው ቢታጠብ ከደዌ ተፈወሰ፡፡ ዮርዳኖስ የጥምቀት ኢዮብ የምዕመናን ደዌው የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ አምሳል ነው፡፡

ኢያሱ ለእሥራኤል ምድረ ርስትን ለማካፈል ሲኄድ ዮርደኖስ ምልቶ አገኘው ከዳር ቆም ቢጸልይ ጌታ ካህናቱን ታቦትን ተሸክማችሁ ቁሙ በላቸው አለው፡፡ ተሸክመው ቢቆሙ የላዩ ወደላይ የታቹ ወደታች የሶስት ቀን መንገድ ሸሸ፡፡ ወተገብሩ ኰሉ ሕዝብ አዲወ ዮርዳኖስ ዬርዳኖስን ለመሻገር ኹሉም አንድ ኹነው ገቡ እንዲል አሥራ ኹለቱ ነገደ እሥራኤል አሥራ ኹለቱ ድንጋይ ይዘው ተሻገሩ ካህናቱ አንዱ እግራቸው ከውስጥ አንዱ እግራቸው ከዳር ሳለ ውሃው አለበሳቸው፡፡ ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት- የካህናቱ እግሮች ተጠመቁ እንዲል መጽሐፈ ኢያሱ 4÷1-19 ኢያሱም ለእሥራኤል ምድረ ርስትን አካፈላቸው ÷ዮርዳኖስ የጥምቀት÷ ኢያሱ የምዕመናን÷ አሥራ ኹለቱን ድንጋይ የአሥራ ኹለቱ ሐዋርያት ምድረ ርስት÷የመንግሥተ ሰማያት አምሳል ነው፡፡

ኤልያስም ዬርዳኖስን ሲሻገር ተማሪዋቹ ተከተሉት፤ ተመለሱ አላቸው፡፡ ቀሩቦ÷ኤልሳዕ ግን መድረሻህን ሳላይ እንዳልመለስ ሕያው እግዚአብሔር ያውቅብኛል አለው፡፡ ኹለቱ ሲኄዱ ዬርዳኖስን ሞልቶ አገኙት፡፡ ኤልያስም መጠምጠሚያውን /መቀነቱን/ እንደ መስቀል አድርጎ ቢመተው ተከፍሎላቸው ተሻገሩ፡፡ የምትወደውን ነገር ለምነኝና ተመለስ ቢለው÷በአንተ አድሮ ያለው መንፈስ ቅዱስ እጽፍ ድርብ ኹኖ ይደርብህ በለኝ አለው፡፡ ድንቅ ነገር ለመንከኝሳ ብሎ ይደርብህ አለው፡፡ አፍራሰ እሳት ሠረገላተ-እሳት መጡለት በነዚህ ሁኖወደ ገነት ሲያርግ÷አባቴ ልጅህን ለምን ጥለኸኝ ትኄዳለህ ብሎ ቢያለቅስበት ዕርገቴን ብታምን ፈጣሪዬ ይደርብህ ባታምን ይቀርብህ ብሎ ሐሜለቱን ጥሎለት ዓረገ፡፡ መጽ.ነገሥ ካልዕ 2÷8-15ዮርዳኖስ የጥምቀት÷ኤልሳዕ የምእመናን ÷ሐሜለቱ የመስቀል÷ገነት የመንግሥተ ሰማያት አምሳል ነው፡፡ ኤልሳዕም መምህሩን ሸኝቶ ቢመለስ ዮርዳኖስን ሞልቶ አገኘው ኤልያስ ሲያደርግ ዓይቶ ኹለት ጊዜ ቢመታው እምቢ አለው፤ በሶስተኛው ኢሀሎኑ ዝየ አምላከ ኤልያስ- የኤልያሰ አምላክ እዚህ የለም? ብሎ ቢመታው ተከፍሎለት ተሻገረ፡፡ ነገሥት ካልዕ.2÷14 ደግሞም ደቂቀ ቤቴልን ሲያስተምር ጸበበነ ማኀደር-ቦታ ጠበበን ቢሉት ዕንጨት ቆርጣችኹ ሰፊ ቤት ሥሩ አላቸው÷ረድኤት እንድትሆነን አንተም አብረኸን ውረድ አሉ፡፡ በጽንፈ ዮርዳኖስ ኾኖ ዕንጨት ሲያስቆርጥ ከተማሮቹ አንዱ የተዋሰው መሳር ወልቆ ቢጥልበት ሞሳሩን ይዞት ወጣ፡፡ ወቀረፈ ኤልሳዕ ቅርፍተ ዕፀ……. ከእንጨትም ቅርፊት ቀርፎ በዚያ ጣለው፤ ብረቱም ተንሳፈፈ፡፡ እርሱም÷እነሆ÷ምሳርህ ውሰደው አለ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው፡፡ ነገሥተ ካልዕ 6÷1-7 ኤልሳዕ የእግዚአብሔር አብ÷ቅርፍተ ዕፅ የእግዚአብሔር ወልድ÷ምሳሩ የአዳም÷ባሕሩ የገሃነመ እሳት አምሳል ነው፡፡ መጥለቅ የማይገባውን ምሳር ይዞት እንደወጣ÷ሞት የማይገባው ክርስቶስ ሞት የማይገባው ክርስቶስ ሞቶ ሞት የሚገባውን አዳምን ከነልጆቹ ለማዳን በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡

ንእማን ሰሪያዊም ለምጽ ቢወጣበት ከደዌዬ ቢፈውሰኝ ብሎ ወርቅ ይዞ ወደ ኤልሳዕ ሲኄድ÷በዬርዳኖስ ታጠብ ብሎ ከመንገድ ስለ ለከበት÷ነቢያ እግዚአብሔር ሲባል በቃሉ ጸለዩ በእጁ ደስ ይፈውሰል ብዬ ነበር እንጂ የውሃ ውሃ ምንአለኝ እንዲሉ÷የውሃ ወሃማ የሀገሬ ወሀዋች ባብና ፋርፋ ምን አሉኝ ብሎ ወደ ሀገሩ ሊኄድ ሠረገላውነ መለሰ፡፡ ሰዎቹ ግን ቢኾን ትፈወሳለህ÷ባይሆን የአገርህ መንገድ ይቀርብሃል ታጠብ አሉት ቢታጠብ ተፈወሰ፡፡ ወርቁን ግሞጃውን ወስዶ ኤልሳዕን እነሆ ዋጋህን ተቀበለኝ ቢለው የእግዚአብሔርን ጸጋ ለወርቅ÷ለብር እሸጠዋለኹን? አልቀበልም አለው፡፡ ነገ ካልዕ 5 ÷6 – 8 ዮርዳኖስ የጥምቀት÷ንእማን የምዕነመናን÷ለምጹ የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ አምሳል ነው፡፡ ይኽን ኹሉ ለመፈጸም በዬርዳኖስ ተጠመቀ፡፡

ትንቢቱን ያናገረ ምሳሌውን ያስመሰለ እሱ ባወቀ ዓይደለምን? ምስጢሩ እንደ ምንድር ነው?ቢሉ፡- አዳምና ሔዋን ከገነት ወጥተው በደብር ቅዱስ ሳሉ ጋትርኤል የተባለ ዲያብሎስ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ ስቃይ አጸናባቸው÷ወዲያው ምትሐቱን ጥቂት ብርሃን አስመስሎ ቢያሳያቸው አንተ ባለ ብርሃን ይህን ጨለማ አርቅልን አሉት፡፡ ስመ ግብርናታችሁን ጽፋችሁ ስጡኝና ላርቅላችሁ ቢላቸው በመከራ ያሉ ናቸውና ይሁንብን ጻፍብን አሉት፡፡ በብራና ብጽፈው ይደመሰሳል÷በእንጨት ብጽፈው ይበሰብሳል ብሎ አዳም ገብሩ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ ብሎ በኹለት ዕብነ ሩካም ቀርጾ አንዱን በዬርዳኖስ አንዱን በሲዖል መካከል ጥሎት ነበርና የአዳምንና የሔዋንን ስመግብርናት በኪደተ ግብሩ ለማጥፋት በዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡ ወደምሰሶ ለነ መጽሐፈ ዕዳኑ የዕዳ ደብዳቤዎቻችንን አጠፋልን እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ቆላ .2÷14

ለፍጥረታት ኹሉ ገዥ ለአብ ምስጋና ለመንግሥትና ለነገሥታት ጌታ ለወልድም ስግደት ልብንና ኩላሊትን ለሚመረምር ለመንፈስ ቅዱስ አኰቴት ይገባል እንበል ለዘላለም አሜን!

ምንጭ -ሰማኒያ አሐዱ መጽሐፍ ቅዱስ ÷ሃይማኖተ አበው÷ መጽሐፈ ምስጢር ዘቅዱስ አባጊዮርጊስ ዘጋስጫ ÷መንገደ ሰማይ ከብፁዕ አቡነ መቃርዬስ ÷የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ÷ትርጓሜ ወንጌል ዘማቴዋስ ÷ወላዲተ አምላክ በብሎይ ኪዳን ክፍል አንድ ከመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ÷ሥርወ ሃይማኖት ከሊቀ ሊቃውንት ኃይለ መስቀል ገብረ መድኀን÷ ዓምደ ሃይማኖት ከብርናኑ ጎበና ÷የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ ክፍል አንድ ከቀ/ዶ/ምክረ ሥላሴ፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ

ኢዩኤል ሰሎሞን ዘደብረ ብሥራት
ጥር 07/05/2004ዓ.ም

No comments:

Post a Comment