Thursday, March 22, 2012

ለመለኮት በሚገባ ልደት ተወለደ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱሰ አሐዱ አምላክ አሜን!
̒ ተወልደ በተድላ መለኮት - ለመለኮት በሚገባ ልደት ተወለደ ̕ቅዱስ ቄርሎስ
በትንቢት የተነገረለት የሰው  ልጆች ጥንተ ተፈጥሮ የፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ አኹን ደግሞ  ሰውን ለማዳን ሰው ኹኖ የተወለደበት ዕለት ነው፡፡  ልደት በየዓመቱ የሚከበረው ታኀሣሥ 29 ቀን ነው፡፡  በዘመነ ዬሐንስ ወንጌላዊ ግን / የሉቃስ ዘመን ጳጉሜን ስድስት ቀናት ስለኾነች ልደት ታኀሣሥ 28 ቀን ይሆናል፡፡  ይኽውም በዓል በሀገራችን በኢትዩጵያ መከበር የተዥመረው በዐፄ ዓምደ ጽዬን ዘመነ መንግስት  በ1 ሺ298ዓ.ም ነው ይባላል፡፡
የጌታ ልደት እንዴት ነበር?
እመቤታችን  ቅድስት ድንግል ማርያም የመውለጃዋ ወራት በደረሰ ግዜ ዓለሙ ኹሉ አንዲጻፍ/አንዲቆጠር / በንጉሥ አውግስጦስ ቄሣር ዘመነ መንግሥት በሮማ ነጉሠ ነገሥት ውስጥ የነበሩት ኹሉ በየትውልድ አውራጃቸወ እየኄዱ አንዲቆጠሩ በወጣላቸው ትዕዛዝ መሠረት ለመጻፍ /ለመቆጠር/  ከጠባቂዋና ከዘመዷ  ከዬሴፍ ጋር ከሰሜናዊው ገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥታ ወደ ደቡቧ ይሁዳ ቤቴልሔም ወደ ምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ተጓዘች፡፡

     እዛም በደረሱ ግዜ ቤተልሔም/ወይቅርዐ/ለመጻፍ/ለመቆጠር/ከየአቅጣጫው  በመጡ የዳዊት ወገኖች ከተማው ተጨናንቆ ነበር፡፡  ማረፊያዎችም ኹሉ በእንግዶች ተይዘው ነበር፡፡  በዚኽም ምክንያት እመቤታችን በእንግዶች ማደሪያ ሥፍራ አላገኘችም፡፡  ነገር ግን ከኹሉ ይልቅ ታላቅ እንግዳ በማሕፀኗ ነበር፡፡  ይኹውም  የጌቶች ጌታ ÷የነገስሥታት ንጉሥ÷  የፍጥረታት ፈጣሪ፣ ሰማይ ዙፋኑ ምድር የአግሩ መረጋጫ የኾነ ኢየሱሰ ክርስቶስ ነው፡፡
በማሕፀኗ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ካስተናገደችው በኋላ ሰዓቱ ሲደርስ ወደ ከብቶች  በረት ገባች፡፡  ትንቢት ይኽን አምልቶና አስፍቶ አሰቀምጦታል፡፡ ትን.ሚክ.5÷2-6
     የከብቶች በረት ለዓይን የሚያስጸይፍ ቢሆንም የትህትና እመቤት ቅድሰት ድንግል ማርያም ይኽን ኹሉ ሳትንቅ የትሕትና አባት የኾነውን ፈጣሪ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስን በድንግልና እንደጸነሰችው ኹሉ በድንግልና ለመውለድ ወጣቲቱ በግ የአንበሳ ደቦሉን ለመውለድ ጉልበቷን ዐጠፈች፡፡  ዘፍ. 49÷9 ያዕቆብ በበረከቱ ውስጥ ስለ ርሱ የጻፈውን ኀያሉን ለመውለድ/ዘፍ.49÷8-12/  ወጣቲቱ ርግብ በድንግልናዋ ውሰጥ ጋደም አለች፡፡ ወጣቲቱ ንስር ታላቁን ንጉሥ በታናሽ ዋሻ ውስጥ ልትወልደው የተወደደችው ጊደር በወጣትነቷ ውስጥ ጋደም አለች /እመቤታችንን በእንቦሳ መስሎ ማስተማር መሥዋዕትኾኖ የቀረበ ልጇ  አካላዊ ቃል ክርስቶስን በቀደምት ሊቃውንት የታወቀ ሲኾን ለምሳሌ ያኽል ነቢዩ ኢሳይያስ 53÷7
መዝሙረኛው ዳዊት በመዝ 68÷31 በመጽሐፈ አርጋኖን ዘሰኑይ ምዕ.9÷37-43 ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓ ገጽ 364 መጽሐፈ መዋሥዕት ዘእግዝዕትነ ማርያም ገጽ54. አባ ጊዬርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ሰዓታት ገጽ 63፤ መጽሐፈ ፀሐይ ገጽ 16 ይኽንን ምስጢር አምልተውና አስፍተዉ በጥልቀት ያስተምሩናል በኀጢአተኞች  ፈንታ መሥዋእት የኾነውን የሠባውን በሬ ልትወልደው የሕፃናት አባት /አሰገኝ /ራሱን በአካለ ሥጋ ወለደ ርሱም ከማሕፀንዋ ወጣ የድንግልና ማኀተም ግን ምንም ሳይኾን ቀረ ወቅቱም የብርድ ስለነበረ ላህምኒ አእመረ ዘአጥረዩ፡፡  አድግኒ ምቅማሆ- በሬ የገዠውን አህያም የጌታውን ጋጣ ዐወቀ፡፡ኢሳ.1÷2የተባለላቸው አንስሳት በትንፋሻቸው አሟሟቁት ፡፡  ለፈጣሪያቸው ተንፋሻቸውን ገበሩ፡፡  ይኽ ኹሉ ነገር የርሱ የልዑል እግዚአብሔር የባለቤትነቱ ድንቅ ሥራ አይደለምን?
ወጠብለለቆ በአጽርቅት- እመቤታችን የምታለብሰው ብታጣ በጨርቅ ጠቀለለችው፡፡ ምስጢሩ ወደ ፊት ዬሴፍና ኒቆዲሞስ እንዲኽ ጠቅልለው ይገንዙኻል ስትል ነው፡፡ ጠቅልላም በከብቶች መመገቢያ ግርግም አስተኛችው፡፡
  በዚያ ምድር አሥራ ኹለቱን ሰዓት ለአራት ተካፍለው መንጋቸውን በሌሊት በትጋት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡ እነኾ ከእግዚአብሔር የታዘዙ መላአክት ለእረኞች ለመንገር በችኾላ ወጡ ፤ እነኾ የምድር ሕያዋን ኾይ የምሥራች ለእናንተ ሲሉ ሰማያውያን ሕያዋንን ተጣሩ ‘ጌታ የኾነው መሲሕ /ክርስቶስ/ በዳዊት ከተማ ለእናንተ በርቶላችኋል’ ሉቃ 2 ÷1-11 በወንጌል እነሆ አዳኙ ለተማረኩት መጣላቸው እነርሱ ግን አላወቁትም /ዮሐ 1 ÷11/ በዚያን ግዜ የጌታ ክብር በዙሪያቸው አበራ፡፡ ከቤተልሔም /ወይቅርዐ/ እነርሱ እስካሉበት ድረስ ባሕረ ብርሃን ፈሰሰላቸው፡፡ ብርሃኑ እንደ መስቀል መብራት ቦግ ብሎ ታየ፡፡
እረኞቹም ይኽን ዐይተው ፈጽመው በመፍራታቸው መልአኩ አረጋጋቸው፡፡ የሕፃኑንም ምልክት ነገራቸው፡፡ ምልክቱ ይኽ ነው፡፡ ወከመዝ ትእምርቱ ለክሙ ትረክቡ ሕፃነ እሱረ መንኮብያቲሁ ወሰኩበ ውስተ ጎል ……… ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታስሮ ታገኙታላችኹ፡፡ ሉቃ .2 ÷12 እንዲኹም ‘ወወለደት ወልዳ ዘበኩራ ወአሠረቶ መንኩባቲሁ……… የበኩር ልጅዋን ወለደች አውራ ጣቱን አሠረችው’ ፡፡ ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ሉቃስ. 2÷7
   እነዚኽ ኹለት ጥቅሶች በመጽሐፍ ቅዱስ ማኀበር የታተመው የዐማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ ገድፎታል / አውጥቶታል/ ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የታተመው የግዕዝና ዐማርኛ ነጠላ ትርጉም ሐዲስ ኪዳን  እና በ2000 ዓ.ም የታተመው ዐዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኘዋለን፡፡
   በድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነጉደው ሲመጡ ተሰሙ፡፡ እረኞቹ እና መንጎቻቸው በሰሙት መልካም ዜና ደስ አላቸው፡፡ ዮም አሐዶ መርዔተ ኮኑ፡፡ መላእክት ወስብእ ከመ ይሰብሕዋ ለክርስቶስ በቃለ አሚን - መላእክት ከእረኞች እረኞች ከመላእክት ጋር አንድ ኾነው አመሰገኑ፡፡ አጥብቀውም አመኑ ፣ ክብርንም ሰጡ፣ እንዲኹም ስጦታዎችን ተሸክመው አመጡ ልበ ንጹሐን፣ ታናናሾች ፣ እውነተኞች ፣ ንጹሐንና ታማኞች የኾኑት፣ እነርሱ ተለይተው መጥተው ዐሥራቱን በኩራቱን በመውሰድ አምጥተው ሰጥተዋል፡፡ እንዲኹም መርጠው ሠውተዋልና ለካህንንነቱ በግ፤ ለሕፃንነቱ ወተት፣ ለንጉሥነቱ ምስጋናን ልባሞቹ ሰዎች አመጡ፣ የመላእክት ሰራዊት ተመሙ፣ ወደዋሻውም ቀረቡ፡፡ ገቡ እና አዩት እጅ መንሻ ይዘውም በፊቱ ሰገዱ፣ እረኞቹ የመዠመሪያውን ዘውድ አበጅተው አቀረቡለት የመንጐቹ ጠቦቶች ለመጣው አማናዊ ጠቦት /በግዕ /ተሰጡት፣ ርሱ በመሥዋት አገልግሎቶቹን ከመሥዋዕትነት ያተርፋቸዋልና መላእክት እና ሰዎች በሕፃኑ ፊት ተሰበሰቡ በአንድ ላይ ተቀላቀሉና ምስጋና ሰጡ፡፡ እግዚአብሔርም በልጅ ልደት ታላቅን ድንቅ ነገር አድርጓል  በታናሽነት ዓለምን ሊዋጅ በመጣው /በልጅ/ ድንግል ፀነሰችው ፣ ማሕፀኗ ተሸከመው፣ ግርግምም አኖረው ታዲያ ሳይደነቅ ስለ ርሱ ማን ሊናገር ይችላል? ፡፡ የእናቱ የድንግል ማርያም ጉልበቶች አጀቡት፣ ክንዶቿ ተሸከሙት፣ ደረቷም ዐቀፈው ከዚኽም የተነሣ አስተዋዮች ይደነቃሉ ይገረማሉም፣ ጡት ይመግበዋል፣ ዋሻ የሙሽርነት መቀመጫ ነው፣ ግርግምም መኝታው ከነዚኽም ጐን ለጐን አእምሮ ደግሞ ተመልክቶት ይደነቅበታል፣ ርሱ በመጠቅለያ ጨርቅ ይጠቀለላል በትሕትናዋ ጡት ይጠባል ይኽን አስደናቂ የልደት ነገርን ሊቁ ቅዱስ
ዮሐንስ አፈወርቅም በአድናቆት ሲገልጸው’ በልዑል ዙፋን ላይ ተቀምጦ ስለ በበረት ተጣለ፣ ሥጋ ሳይኾን የነበረ የማይዳሰስ ወልድ ዋሕድ ዛሬ ሥጋን በመዋሐድ ተዳሰሰ ፣ ኀጢአትን ይቅር የሚል ርሱ በጨርቅ ተጠቀለለ’ በማለት ገልጾታል፡፡ ርሱ እሳትን ይለብሳል ግን ደግሞ ሠረገላዎቹን በታታሪነት ያሽከረክራል፡፡ ሃይ አበው ዘ ዮሐንስ አፈወርቅ ምዕ 66 ÷4፤ ሕዝ 1 ÷ 15 -21 
     ታዲያ ይኽ የባለጠጋው /የአብ /ልጅ ትሕትና ምክንያቱ ይምን ይሆን? ማንም ሊጠቀም የሚሻ ሰው በፍቅር ይስማ፣  ታላቅ እና ዘላለማዊ የኾነው ወልድ ለምን ወደታች መጣ፣ ያውም በሥጋ ልደት ለኹለተኛ
ጊዜ?  ከሠረገላ ወርዶ በግርግም ለመቀመጥ ምክንያቱ ምን ይኾን?  ከክብር ግርማ ወደ አነስ ኹኔታ ይወርድ ዘንድስ ለምን ወደደ?  ድንቅ አምላክ ርሱ ራሱን ለማሳነስ ወደደ /ፊለጵ 2፣7-8/
     ይኽን የመደነቅ ጥያቄ ቅዱሳን መላእክትም ሢያነሱና ሲደነቁ ኖረዋል፡፡  ሰው እንደ እንሰሳት በኀይለ ዘርዕ /በዘር በሩካቤ/ ይራባል፣  እንደ መላእክትም ደግሞ አዋቂ ነው፡፡ እንስሳት ቢራቡ አያውቁም፣ መላአክትም ቢያውቁ አይራቡም ስለዚኽ አኹንም ኀይለ ዘርዕን ከእውቀት አስተባብሮ  የያዘ ከሰው በቀር ሌላ ፍጥረት አላዩምና በእውነት አግዚአብሔር  ለሰው ያለው ፍቅር ምንኛ የበዛ ነው እያሉ ሰለ እኛ እነርሱ ምስጋና አብዝተው አቀረቡ፡፡  መጽሐፍስ  ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው ? መዝ.8÷10 በማለት ቅዱስ ዳዊት ገልጾታል፡፡  ጠቢቡ ሰሎሞንም በእኔ ላይ ያለው ዓላማዉ ፍቅር ነዉ……. በዘቢብም አጽናኑኝ ፣ በእንኮይ አበረታቱኝ ፣ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለኹና መሐ. 2፣4-5 በማለት አግዚአብሔር ለሰው ልጅ ምንኛ አስደናቂ ፍቅር እንዳለው በመረዳት ገልጸውታል፡፡  በዓሉ የሰላምና የፍቅር ይኹንልን ለዘላለሙ አሜን፡፡
ምንጭ፡-2000.ምየታተመውዐዲሱሰማኒያ አሐዱ መጸሐፍ ፣ሃይማኖተ አበው ፣የእግዚአብሔር መንግሥስት ታሪክ በምድር ላይ አንደኛ መጽሐፍ ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ፣የቤተክርስቲያን ታሪክ በኢትዩጵያ አባ ጎርጎርዩስ ፣የክርስቶሰ አሰደናቂ የልደት ምስጢር በቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግ ድርሳን በመጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ፣ወላዲተአምላክበብሉይ ኪዳን ክፍል ኹለት በመጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ ፣ወላዲተአምላክበመጽሐፍቅዱስዲ/ን እሸቱ ታደሰ እና በዲ/ን ደጀኔ ሽፈራው

                 ይትባረክ እግዚአብሔር አምላክ አበዊነ

 ኢዩኤል ሰሎሞን ታኀሣሥ 2004 ዓ.ም (ደብረ ብሥራት)


1 comment:

  1. የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
    እነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.

    ReplyDelete